በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር የተዘጋጀው የጋሞኛ ቋንቋ ኤሌክትሮኒክ መዝገበ ቃላት መተግበሪያ የዩኒቨርሲቲውና የዞን አመራሮች፣ መምህራን እና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት ሚያዝያ 12/2015 ዓ/ም ይፋ ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝትና ቴክኖሎጂ ማበልጸግ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በቋንቋው መስክ የሚደረጉ ምርምሮች የሚጠቀሱ ሲሆን በጋሞኛ ቋንቋ ላይ እየተከናወነ ያለው ምርምር ወደ አንድ እርምጃ አድጎ የጋሞኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት የሞባይል መተግበሪያ መፍጠር ተችሏል፡፡

ቴክኖሎጂ መረጃን በቀላሉ ለመቀበልና ለማሰራጨት ብቻ ሳይሆን የቋንቋን ተደራሽነት ለመጨመር እንዲሁም ቋንቋን ለማዳበርና ለመጠበቅ በእጅጉ እንደሚረዳ የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ የቋንቋ መማሪያዎች፣ ኦንላይን መዝገበ ቃላትና የትርጉም ሶፍትዌሮች ሰዎች ቋንቋን እንዲማሩና እንዲረዱ ከማድረግ በተጨማሪ ቋንቋን ለመሰነድና በአግባቡ ይዞ ለማቆየት በሚደረገው ጥረት ላይ ዓይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት በሚያወጣው ዓመታዊ የማኅበረሰብ ጉድኝት ፕሮጀክቶች ጥሪ መሠረት የሚቀርቡና በግምገማ ጸድቀው የሚደገፉ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትና ቁጥር እየጨመሩ ከመምጣታቸው በሻገር ውጤትም እያስመዘገቡ ስለመሆኑ በጋሞኛ ቋንቋ ኤሌክትሮኒክ መዝገባ ቃላት መተግበሪያ ዝግጅት ፕሮጀክት ላይ የተገኘው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ ፕሮጀክቱ በ2013 በጀት ዓመት የጸደቀና በወቅቱ ከጸደቁ ሌሎች 25 ፕሮጀክቶች አንዱ የነበር ሲሆን በፕሮጀክቱ የተገኘው ውጤትም በተለይ በማኅበረሰቡ ውስጥ በጋሞኛ ቋንቋ ለመናገር ለሚቸገሩና  ቋንቋውን ያለ አስተማሪ ለመማር ለሚፈልጉ እንዲሁም ጋሞኛን እንደ ትምህርት ቋንቋ ለሚጠቀሙ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የቋንቋ ዓይነቶችና አገልግሎታቸው፣ የመዝገበ ቃላት ዓይነቶች፣ የጋሞኛ ቋንቋ ታሪካዊ ዳራ፣ አወቃቀርና አሁን የደረሰበት የእድገት ደረጃ፣ በቋንቋው የሚታዩ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የፕሮጀክቱን ሥራ ከመነሻው እስከ ማጠቃለያው የሚያብራራ ጽሑፍ በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ በሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ጎንደሬና መተግበሪያውን ባዘጋጀው የዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አቶ ጌታሁን ትዕግሥቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አቶ ጌታሁን ከዚህ ቀደም በጋሞኛ ቋንቋ ላይ የተሠሩ መተግበሪያዎች አለመኖራቸውን ጠቅሰው በዩኒቨርሲቲው የጋሞኛ ቋንቋ ት/ክፍል ተገምግሞ በቀረበው መሠረት መተግበሪያውን ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታሁን መተግበሪያው 4,990 ቃላትን የያዘ ሲሆን ጋሞኛን ወደ አማርኛ፣ ጋሞኛን ወደ እንግሊዝኛ፣ እንግሊዝኛን ወደ አማርኛና እንግሊዝኛን ወደ ጋሞኛ መተርጎም የሚያስችል ነው፡፡ የፕሮጀክት ሥራውን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት የፈጀ ሲሆን በቅርቡ በጉግል ፕሌይ ስቶር ላይ ተለቆ 300 ያህል ተጠቃሚዎች ጭነው እየተጠቀሙ ነው፡፡ በቀጣይም ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት