የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ በተለያዩ ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ሚያዝያ 30/2015 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ቦርዱ የዩኒቨርሲቲውን ዕቅድና የሥራ አፈፃፀም መገምገምን ጨምሮ ተቋሙን ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚያስችሉ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የዕለቱ የውይይት መድረክም ለቦርዱ ያልታዩ ተቋማዊ ችግሮችን ማኅበረሰቡን በማወያየት ለማወቅ፣ ተቋሙ ምን ላይ መታገዝ እንዳለበትና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን የሚጠቁሙ ሃሳቦችን ለመሰብሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሀብታሙ ጠቅሰዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን የመምህራን መብትና ጥቅማ ጥቅም በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑና በመምህራን የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እያገኙ አለመሆኑ፣ መምህራንንና ሙያቸውን ለማክበር በሚያስችል ደረጃ ኑሯቸውን ለማሻሻል መንግሥት በቀጣይ ለመፈጸም ከገባቸው የደመወዝ ጭማሪና ሌሎች ተስፋዎች አንጻር ምን እየታሰበ ስለመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን በቂ ዝግጅትና ድጋፍ እያደረገ ስለመሆን አለመሆኑ፣ የአስተዳደር ቦርዱ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ባሻገር ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና የግንኙነት አማራጮችን መፍጠር ስለማስፈለጉ፣ የመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት በቀጣይነት ሊሠራ አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ የተለያዩ ለመማር ማስተማርና ለምርምር ሥራ የሚያገለግሉ የICT ቴክኖሎጂዎችንና ሶፍትዌሮችን በግዥ ማሟላት ስለማስፈለጉ፣ ለ3 ዲግሪ ተማሪዎች የሚሰጠው የምርምር በጀት በቂ አለመሆኑና ማስተካከያ እንዲደረግ እንዲሠራ ስለመፈለጉ፣ በወቅታዊ ሀገራዊ የበጀት እጥረት ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ሁሉም የሥራ ዘርፎች ላይ ጫና ስለመፈጠሩና ስለቀጣይ መፍትሔዎች፣ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ግንባታ ስለመጓተቱ፣ ከመምህራን የቤት አበልና ከሌሎች መምህራን ከሚከፍሉ ክፍያዎች ላይ የሚቆረጠው 35 በመቶ የግብር ተቀናሽ ተገቢ ስላለመሆኑና በሀገራችን የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው ክፍል ብቻ ከሚገባው በላይ ግብር ከፋይ መደረጉና ከንግዱ ማኅበረሰብና ሌሎች ዘርፎች የግብር አሰባሰብ ፍትሐዊ ስላለመሆኑ፣ በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ቤተ-ሙከራዎች ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ስላለመሆናቸውና ወቅቱን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመግዛት የቦርዱ ድጋፍ ስለማስፈለጉ፣ ከኃላፊ ምደባና የተለያዩ ሹመቶች ጋር በተያያዘ በቅርብ ኃላፊ የሚሰጠው ውጤት ፍትሐቂ አለመሆንና ሌሎች ችግሮች ስለመኖራቸው የሚያትቱ ሃሳቦች በዕለቱ ከተነሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ራስ ገዝ ከመሆን ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲው ኮሚቴ በማወቀር የዝግጀት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸው የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ግንባታ ሊዘገይ የቻለው ግንባታውን በሚያከናው ተቋራጭ ድርጅት ችግር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቤተ-ሙከራዎችን ከመዘመንና ከማደራጀት አንፃር ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ በቅርቡም ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የፊዚክስ ቤተ-ሙከራን ማደራጀት መቻሉንና ለሌሎች ዘርፍ ቤተ-ሙከራዎች የሚውሉ ቁሳቁሶች ግዥም እየተፈጸመ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረው የበጀት እጥረት ጊዜያዊና እንደ ሀገር የገጠመ ችግር መሆኑንም ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡ ከኃላፊ ምደባ ሹመት ውድድሮች ጋር ተያይዞ በቅርብ ኃላፊ የሚሰጠው ነጥብም ከመደብ ሥራ ባህርይ ጋር የተያያዘና ሥራውን ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ተወዳዳሪዎችም ሆኑ ጠያቂዎች በዚሁ አግባብ እንዲገነዘቡ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል አቶ ፈጠነ ተሾመ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ከሚገኙ አንጋፋ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ ተቋሙን ትራንስፎርም በማድረግ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ዕይታ ለመጨመር ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቦርዱ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከበጀት አንፃር የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ፈጠነ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቦርዱ በትብብር ይሠራልም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በሰጡት ማጠቃለያና ምላሽ እንዳመላከቱት ተቋሙ የተሻለና ተማሪዎች መርጠው የሚማሩበት ተቋም ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው አመራርና ማኅበረሰብ መካከል የጋራ ራዕይና መግባባት እንዲኖር ቦርዱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በቀጣይ የሰው ኃይል ማልማት፣ ግልጸኝነት መፍጠር እንዲሁም የበጀት ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲሠራ ቦርዱ እገዛ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶ/ር ሀብታሙ ከታክስ ጋር ተያይዞ የቀረቡት ጥያቄዎች የሕግ ምላሽ የሚፈልጉ በመሆናቸው ችግሩን ለሚመለክተው አካል እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡ ከኑሮ ውድነትና ከደመወዝ ጋር ተያይዘው የተነሱ ሃሳቦችም ተገቢ መሆናቸውን ያወሱት ዶ/ር ሀብታሙ ጥያቄዎቹ በሀገራዊ ማዕቀፍ ሊመለሱ የሚችሉ መሆናቸውንና አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ቦርዱ ተቋሙንና የተቋሙን ማኅበረሰብ በተሰጠው ኃላፊነትና በሚችለው አቅም ለማገዝ እንደሚሠራ የጠቆሙት ዶ/ር ሀብታሙ በቀጣይ በሚደረጉ የቦርድ ስብሰባዎች ላይ የመምህራንን ድምጽ ለመስማት እንዲቻል የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተወካዮች እንዲሳተፉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት