በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሽናል ፈተና ማእከል በማቋቋምና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ የአሠልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ዙሪያ ከአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጋር ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም ውይይት ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እንደመሆኑ በሀገራችንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የሥራ ቋንቋ ቢሆንም በቋንቋው አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ ከፍተት ለመሙላት ከዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማእከልና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ለእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና በመስጠት በቀጣይ ደግሞ ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለጻ ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሽናል ፈተና ማእከል መቋቋሙ በዩኒቨርሲቲው የሚያስተምሩ መምህራንና ተማሪዎች ወደ ውጭ ሀገር የመውጣት ዕድል ሲያገኙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የፕሮፌሽናል ፈተና ውጤት ስለሚጠይቅ ፈተናውን በዩኒቨርሲቲው ማዕከል በመፈተን የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ ያስችላል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል አስተባባሪ ዶ/ር አባተ አንጁሎ በሰጡት አስተያየት እንግሊዝኛ ቋንቋ በጣም አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ላይ ነው ያለነው ያሉት አስተባባሪው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ሥልጠና መሰጠቱ መምህራን የግል ከሂሎታቸውን በማዳበር ለተማሪዎቻቸው የተሻለ ዕውቀት እንዲያስጨብጡ፣ ወደ ውጭ ሀገር ለመውጣት ዕድል ሲያገኙም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሽናል ፈተና በቀላሉ ማለፍ እንዲችሉ፣ ተማሪዎች  እንግሊዝኛ ቋንቋ አቀላጥፈው መናገርና የቋንቋውን ሰዋሰው ጠብቀው መጻፍ እንዲችሉ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ መረጃዎችን መረዳት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህርና የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማእከል አስተባባሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ በበኩላቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ የዩኒቨርሲቲያችን የመማር ማስተማሪያ ቋንቋ እንደመሆኑ ማእከላችን ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል፡፡ ዶ/ር መለሰ ማእከሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሽናል ፈተና ማእከል ሲቋቋምም ፈተናውን ለሚወስዱ ተፈታኞች የዝግጅት ሥልጠና የመስጠት፣ ፈተና የማዘጋጀት፣ ለ2ና 3 ዲግሪ ተማሪዎች ተጨማሪ ሥልጠና የመስጠት እንዲሁም በሁሉም ካምፓሶች ለሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች የክፍል ውስጥ እንግሊዝኛ/Classroom English/ የአሠልጣኞች ሥልጠና የመስጠት ተግባራትን በማከናወን መምህራንና ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ አራቱም ክሂሎቶች አጠቃቀም የተሻሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞን ጨምሮ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የምርምር ዋና ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንዲሁም  የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ  የትምህርት ክፍሉ ኃላፊና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማእከል አስተባባሪ ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት