የ45 ቀን ዕድሜ ያላቸው 2,000 ሳሶ ብሮይለር ብሪድ/Saso Broiler Breed/ ዝርያ ጫጩቶችን በመረከብ ሥራ የጀመረው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል ከሚያዝያ 24/2015 ዓ/ም ጀምሮ 1,800 የእርድና እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለሽያጭ አቅርቦ እየሸጠ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለዶሮ እርባታ በዋናው ግቢ ሦስት ሕንጻዎች ያሉት ጣቢያ የከፈተ ሲሆን የእርድና እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ለማርባት የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ዶሮዎቹ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገላቸው ክትባትና አስፈላጊው ሕክምና እንደሚሰጣቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ሳይንስና ዶሮ እርባታ ላይ የሚያጠኑ ከመጀመሪያ እስከ 3 ዲግሪ ተማሪዎች ምርምር መሥራት እንዲችሉም ጭምር ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ልምድ ለመውሰድና ለምርምር ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው በማእከሉ መጠቀም ይችላሉ ብለዋል፡፡

በማእከሉ የእንስሳት ጤና ተመራማሪ ዶ/ር መስፍን ሹሩቤ 500 ሴት ዶሮዎችና 1,300 ወንድ ዶሮዎች በአጠቃላይ ለእርድና እንቁላል ለመጣል የደረሱ 1,800 ዶሮዎች ከ300-550 ብር ዋጋ ለሽያጭ መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በተካሄደው የሽያጭ ሂደት ከ300 በላይ ዶሮዎች መሸጣቸውን ተመራማሪው ጠቁመው ዶሮዎቹን ለመግዛት የሚፈልጉ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል ወይም የምርምር ዳይሬክቶሬት በማነጋር ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡ በቀጣይ 3,000 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት የዶሮና እንቁላል ገበያን ባማከለ መልኩ በሰፊው ለግቢው ማኅበረሰብ ለማቅረብ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት