አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ ዛባ ቀበሌ በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ግንቦት 16/2015 ዓ/ም የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ እጅግ ማዘናቸውን በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም ገልጸው በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ ተይዞ ችግሩን መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ይሠራል ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ዕቅድም በገንዘብ ሲተመን 300 ሺህ ብር የሚያወጣ 70 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች ጋር በመወያየት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

የኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢልቶ ኢፀና አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖች፣ ቀይ መስቀል፣ ሌሎች ግብረ ሠናይ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምግብ ድጋፍ ያደረጉ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ስላደረገው ድጋፍና በቀጣይ ለመሥራት ስላስቀመጣቸው ሐሳቦች አመስግነዋል፡፡ በአደጋው 2,167 አባወራዎች ተጎድተዋል ያሉት አስተዳዳሪው ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ያህል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔና ሌሎች የጋራ የባንክ አካውንት በመክፈት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ባሰባሰቡት 170 ሺህ ብር 210 የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 20 ፓኬት ሚስማር እንዲሁም ከተለያዩ የሃያማኖት ተቋማትና ሌሎች ግለሰቦች የተሰበሰቡ 130 ሺህ አልባሳት ጨምሮ በአጠቃላይ 280 ሺህ ብር የሚገመት ቁሳቁስ አበርክተዋል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን በቀጣይም ተጎጂዎች መቋቋም በሚችሉበትና ችግሩ በዘላቂነት በሚፈታበት ሁኔታ  ላይ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የቀበሌው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰሎሞን ታከለ በደረሰባቸው የጎርፍ አደጋ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውና መምህራኑ ባደረጉት ድጋፍ መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ሰሎሞን የውኃ መውረጃው እስከ አሁን ባለመስተካከሉ ዝናብ ሲዘንብ በስጋት ወደ ተራራው ወጥተው የሚያድሩ በመሆኑ መንግሥት ችግሩን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

በድጋፍ መርሃ ግብሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የሳውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔናና ሌሎች የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢልቶ ኢፀና እና የጎፋ ዞን አመራሮች ተገኝተው ተጎጂዎቹን አጽናንተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
For more Information Follow us on:-
Website - https://www.amu.edu.et/
Telegram - https://t.me/arbaminch_university
Facebook - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
YouTube - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት