አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Enhancing Community Development Pertaining Education, Production and Product Access through Integrated Intervention/ECoD›› በተሰኘ ግራንድ ምርምር ፕሮጀክት በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ የሚሠራው የመንገድ ሥራ የመስክ ምልከታ ግንቦት 16/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት የ“ECoD” ግራንድ ምርምር ፕሮጀክት በመሎ ኮዛ ወረዳ ላሃ ከተማ በቅርብ ርቀት ያሉ ቀበሌያትን በመንገድ ያስተሳሰረ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጀመር የተመደበው አንድ ሚሊየን ብር በቂ ባለመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪ የ600 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ዳይሬክተሩ ወረዳው እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የቱሪዝም መስህብ ያለው በመሆኑ በኮይሻና ሌሎች መሰል በአካባቢው ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ ተማሪዎች ለልምምድ እንዲወጡ  እንዲሁም በመሎ ኮዛና በቁጫ ወረዳ የማዕድን አለኝታ ጥናት የሚያካሄዱ ተማራማሪዎችን በመላክ ሌሎች ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤልያስ በበኩላቸው አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ቢሆንም የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ገልጸው ፕሮጀክቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ ሥራ፣ የተዘጉ ት/ቤቶችን በማስከፈትና ከመንገድ ርቀው ያሉ ት/ቤቶችን ከመንገድ ጋር በማገናኘት የሚበረታታ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የወረዳው መንግሥት የማኅበረሰብ ንቅናቄ ፈጥሮ ከአርሶ አደሩ ገንዘብ በማሰባሰብና ከወረዳው መንግሥት በጀት ድጋፍ በማድረግ ለማሽን ኪራይና ነዳጅ ግዥ በመፈጸም ከፕሮጀክቱ ጋር በትብብር በመሥራት ውጤት እያዩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ቤታ ጻማቶ ፕሮጀክቱ በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ በትምህርት፣ ጤና፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ምርትን ወደ ገበያ ማቅረብ፣ አእምሮ ውቅር (Mind Set)፣ ሥራ ፈጠራና መንገድ ዝርጋታ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በወረዳው ስድስት ትምህርት ቤቶች በፕሮጀክት ታቅፈው የአእምሮ ውቅር ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና የመንገድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶ/ር ቤታ ጠቁመዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው በወረዳው በቦክሬና ቶባ ቀበሌያት 24 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ዝርጋታ የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ቀበሌያት እየተስፋፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡

የመሎ ኮዛ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘማች ጌታቸው በበኩላቸው በፕሮጀክቱ፣ በወረዳው አስተዳደር ድጋፍና በአካባቢው ማኅበረሰብ ተሳትፎ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ ሁለት ቀበሌያትን በሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚገኙ ሦስት ዋና መንገዶች ጋር የሚያስተሳስር የ24 ኪ.ሜ መንገድ ሥራ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ወጪም ከወረዳው አስተዳዳር 8,495,000.00 ብር በመቶኛ 54.1%፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በጥሬ ገንዘብና በጉልበት 3,112,250.00 በመቶኛ 19.8%፣ ከሳልኒ ዊ ቢዩልድ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት/Salini Webuild Construction PLC/ 2,500,000.00 ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ  በመቶኛ 15.9% እና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 1,600,000.00 ብር በመቶኛ 10.2% የሚሸፈን ይሆናል፡፡ የፕሮጀክቱ የእስከ አሁን ወጪ 15,707,500.00 ብር የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ለሚሠሩ የስትራክቸር፣ የግሬደርና ጠጠር ማልበስ ሥራዎችም ሰፊ ድጋፍ የሚጠበቅ መሆኑን አቶ ዘማች ጠቁመዋል፡፡

ጉብኝት የተደረገበት የመንገድ ሥራ የአፈር ሥራው (Earth Work) 75 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት የ“ECoD” ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ተማራማሪና የወረዳው አስተባባሪ አቶ ባሕሩ ባይከዳኝ የዲች ጠረጋ፣ በሦስት ቦታዎች የስትራክቸርና የውኃ መውረጃ ቱቦዎች ቀበራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ አንድ ድልድይና 10 ቱቦዎችን የመቅበር ሥራዎች የሚቀሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ባሕሩ መንገዱ ሲጠናቀቅ በሁለት ቀበሌያት የሚገኙ 15 ሺህ አባወራ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሎ ኮዛ ወረዳ የቶባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አድማሱ አደሬ በሰጡት አስተያየት በመንገድ ችግር ምክንያት ምጥ የተያዙ እናቶችን ሐኪም ቤት ለመውሰድ፣ ያመረቱትን ምርት ገበያ አውጥተው ለመሸጥ፣ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክና ቀለብ ለማድረስ ሲቸገሩ መኖራቸውን ተናግረው መንገዱ በመሠራቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ለመንገድ ሥራው ወረዳው ለእያንዳንዱ አባወራ አንድ ሺህ ብር የወሰነ ቢሆንም በፈቃዳቸው 10 ሺህ ብር መደገፋቸውን ያስታወሱት አቶ አድማሱ ኅብረተሰቡ ለመንገድ ሥራው ሲባል መኖሪያ ቤቱ ሲፈርስና ማሳው ሲወሰድ ቅሬታ ያላሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምልከታው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ቤታ ጻማቶ፣ የመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤልያስና ሌሎች የወረዳና የቀበሌ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት