Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎክን የመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል ከበጎ አድራጎት ማዕከል ጋር በመተባበር  በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ ልማት እና አርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለማረሚያ ብሩህ ተስፋ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ለሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ከተለያዩ አካላት በልገሳ ያገኟቸውን የመማሪያ ማጣቀሻ መጻሕፍት እና አልባሳት ድጋፍ ግንቦት 22/2015 ዓ/ም  አበርክተዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የዩኒቨርሲቲው የበጎ አድራጎት ማዕከል ላለፉት በርካታ ዓመታት ለትምህርት ቤቶች መቀመጫዎችን፣ ጥቁር ሠሌዳዎችንና ሌሎች መሰል ግብዓቶችን በማበርከት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ማዕከሉ አድጎ ተቋማትን በመደገፍ ላይ መሆኑ በቀጣይ ወደ ትምህርት ማዕከላት የማይመጡ ወጣቶችን ባሉበት ለመርዳት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ተግባር መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው የኢንፎክን እና በጎ አድራጎት ማዕከላት በቅንጅት ላደረጉትም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን በጋራ በመደገፍ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚሠሩም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንፎክን የመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል አስተባባሪ የሆነችው የአርክቴክቸር 5ኛ ዓመት ተማሪ ሠላም ዳኛቸው በበኩሏ ኢንፎክን በመጻሕፍት እጥረት ምክንያት የመረጃ እጥረት እንዳይከሰት በዶርም ውስጥ በመዋዋስ ያነቡ በነበሩ ሰባት ተማሪዎች በ1999 ዓ/ም የተቋቋመ ክለብ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አድጎ ወደ ማዕከልነት መለወጡን ተናግራለች፡፡ ተማሪ ሠላም ከአዲስ አበባ ብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጄንሲ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ከ9ኛ- 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች የሚያገለግሉና በእርዳታ የተገኙ 23,400.00 ብር የሚገመቱ መጻሕፍትን አከፋፍሎ ያበረከተ ሲሆን 112 ከ5ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለሚገኙ ተማሪዎች የሚሆኑ የማጣቀሻ መጻሕፍትን ለከተማው የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣  67 የማጣቀሻ  መጻሕፍትን ለልማት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣  82 የሕግ፣ የታሪክ፣ የሥነ-ልቡናና አነቃቂ መጻሕፍትን ለማረሚያ ብሩህ ተስፋ እና 119 ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሆኑ የተፈጥሮና የማኅበራዊ ሳይንስ ማጠቃሻ መጻሕፍትን ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የአልባሳት ድጋፍ ለልማትና ለማረሚያ ብሩህ ተስፋ መሰጠቱን ገልጻለች፡፡

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ መምህር አቶ ስለሽ ካሣ፣ የማረሚያ ብሩህ ተስፋ ትምህርት ቤት  ርዕሠ መምህር አቶ አዳነ አርባ እና የልማት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ መምህር አቶ ታደለ ታምሩ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቦጋለ ቦቾ በሰጡት አስተያየት የተደረገው ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለውን የመጻሕፍት እጥረት በመቀነስና የተማሪዎችን የዕውቀት ክፍተት በመሙላት ውጤታቸውን እና ሥነ-ምግባራቸውን የሚያሻሽል ከመሆኑም በላይ ትምህርት ቤቶቹን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የሚያቆራኝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ እየተከናወነ ላለውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ለኢንፎክን የመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት