የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል የደረጃ ዶት ኮም እህት ኩባንያ/Dereja.Com Sister Company/ ከሆነው ኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ‹‹Infomind Solutions›› እና ከጋሞ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ለተመረቁ ወጣቶች ከነሐሴ 26/2015 ዓ/ም  ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ወራት ሲሰጥ የነበረው በ‹‹Dereja Academy Accelerator Program›› ክሂሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ኅዳር 2/2016 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደረጃ ዶት ኮም እህት ኩባንያ ከሆነው ኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ጋር በመተባባር ላለፉት ሦስት ዓመታት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ስለ‹‹Dereja Academy Accelerator Program›› ሥልጠና በመስጠት አብዛኛዎቹን ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በ2015 ዓ/ም 197 አዲስ ተመራቂ ወጣቶችን በማሠልጠን ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጓቸው ተጨማሪ ክሂሎቶች እንዲኖሯቸው የማስቻል ሥራ መሠራቱን አስተባባሪዋ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አስተባባሪዋ በበይነ-መረብ (Online) እና በለርኒንግ ማኔጅመንት ሲስተም (Learning Management System/LMS) የሚሰጠውን ሥልጠና አጠናቀው ከኅዳር 6/2016 ዓ/ም ጀምሮ ሙያዊ ክሂሎት ከሚባሉት ከሰባቱ አንዱን በመምረጥ ከባለሙያው ጋር ተገናኝተው ሲወስዱ የምስክር ወረቀት የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱ ሠልጣኞች ካልወሰዱት ይልቅ ለሥራው ቅርበት የሚኖራቸውና የተሻለ የሥራ ዕድል የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ሠልጣኞች የሥልጠናውን ክሂሎት በአግባቡ በመጠቀም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መ/ርት ስለእናት አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲንና የደረጃ አካዳሚ ዋና አሠልጣኝ መ/ር አድማሱ ጣሰው እንደገለጹት የሥልጠናው የመጀመሪያ ክፍል ሰዋዊ ክሂሎት (Soft Skill) በሚባሉ፡- የአመራርነት፣ ተግባቦት፣ ራስን ማወቅ፣ ገጽታ ግንባታ፣ ውጤታማ የሆነ ዕቅድ አወጣጥ፣ የጊዜና ገንዘብ አጠቃቀም፣ ሁሉን አቀፍ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ውጤታማነትን የመፈለግና የተቀጣሪነት ክሂሎት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ከሙያዊ ክሂሎች መካከል አንዱን በመምረጥ ሥልጠና እንደሚወስዱና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባለቸው ባለሙያዎች ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግላቸው አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡ የሥልጠናው ዋና ዓላማ አቅምን በመገንባት የተቀጣሪነት ክሂሎትን ማሳደግ እንደመሆኑ ሥልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው የምስክር ወረቀት የሚያገኙ ሠልጣኞች ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እንደሚመቻች መ/ር አድማሱ ጠቁመዋል፡፡

በ2015 ዓ/ም ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምኅንድስና የተመረቀችው ሠልጣኝ ማርታ ማይሳ ሥልጠናው እንደ አዲስ ተመራቂ ጠቃሚ ክሂሎቶችን ያገኘችበት መሆኑን ተናግራ በለርኒንግ ማኔጅመንት ሲስተም በተሰጡት ኮርሶች ሞጁሎችን ሲጨርሱ ፈጣን ግብረ መልስ የማያገኙ መሆኑ ቀጣይ የሚሠጡትን ሞጁሎች ለመከታተል አስቸጋሪ ስለሚያደርግ መስተካከል ቢችል የሚል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

በ2015 ዓ/ም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ የተመረቀው ወጣት አማኑኤል ያዕቆብ በበኩሉ ሥልጠናው የሥራውን ዓለም ለማያውቁ መሠረታዊ ዕውቀት የሚያስጨበጥ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት