Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞው የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ባደረገው የማዕድን አለኝታ ጥናት በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ከ950 ሚሊየን ቶን በላይ የብረት እንዲሁም 429 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ከምችት መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና በመሎ ኮዛ ወረዳ የተደረገው የማዕድን አለኝታ ጥናት የተመራማሪዎች ቡድን መሪ መ/ር አገኘሁ ቦርኮ ጥናቱ በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ የሚገኝን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት መጠን፣ ጥራትና ማዕድናቱ ያሉበትን ቦታ ለማወቅ የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ  ስድስት  ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በሥራው ላይ የጆኦ-ኬሚስትሪና ጂኦ ፊዚክስ መረጃዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለፃ በወረዳው ጋዘር በተሰኘ ቀበሌ በ146 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ በተደረገ ጥናት ከ950 ሚሊየን ቶን በላይ የብረት እንዲሁም በዚሁ ወረዳ ባንካ ቀበሌ 429 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት መኖሩን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ የብረት ማዕድን አምስት ደረጃዎች ያለው ሲሆን በስፍራው የተገኘው የብረት ማዕድን ደረጃ 3 ላይ የሚመደብ እንደሆነም መ/ር አገኘሁ ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ የተደረገው በውስን ቦታ ላይ እንደሆነ የተናገሩት ተመራማሪው በአካባቢው በስፋት መሰል ጥናቶች ማድረግ ቢቻል ወደ ባስኬቶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ኮይሻ አካባቢዎች መሰል የማዕድን ክምችቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምልክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተመራማሪው እንደ ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መሰል ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የሰው ኃይል እና የተሟሉና ዘመናዊ የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎች ያሉ መሆኑን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በርካታ የሚጠኑ አካባቢዎችን በትኩረት ለመሥራት በትምህርት ክፍል ደረጃ ከፍተኛ ፍላጎትና ዕቅድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የትብብር ግንኙነት አለኝ ብሎ ከሚጠቅሳቸው የሀገር ውስጥ ተቋማት መካከል አንዱ ከቀድሞው የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ሲሆን ከተቋሙ ጋር በማዕድንና ባዮ ጋዝ ልማት ዘርፍ ላይ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡  የማዕድን ዘርፍ ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት የልማት ምሶሶዎች ብላ ከለየቻቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያከናወናቸው የማዕድን አለኝታ ጥናቶች ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫ ጋር የተዛመዱ ናቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥናት ባካሄደባቸው ቦታዎች የተገኙ የማዕድን ክምችቶች ሀገራችን በዘርፉ ከፍተኛ ሀብት እንዳላት ያመላከቱ መሆናቸውን የጠቆሙት  ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በጥናቶች የተገኙ ማዕድናት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ እነዚህን ማዕድናት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣን የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረትና የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር እንዲሁም የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንደሚሠራ ተቋም  መሰል በማዕድን ዘርፍ የሚከናወኑ የጥናትና የልማት ሥራዎችን በስፋት መሥራት ቀጣዩ ዕቅዳችንና በትኩረት የምንሠራበት መስክ ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ለዚህም ሥራ ይረዳ ዘንድ ዩኒቨርሲቲው የጂኦ ሳይንስ ምርምርና ልማት ማዕከል /Geo-Science Research and Development Center/ ለማደራጀትና ዘርፉን ተጨማሪ የልኅቀት አማራጭ ለማድረግ እየሠራ  መሆኑን አውስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ስድስት ዓመታት ከቀድሞው ደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በቡርጂ፣ በጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ስምንት የማዕድን ጥናት ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ቶሌራ በአጠቃላይ ከሁለቱ ተቋማት ስምንት ሚሊየን ብር ተመድቦላቸው በተከናወኑ በነዚህ የማዕድን አለኝታ ጥናቶች በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ “Quartz”፣ “Feldspar”፣ “Aquamarine”፣ “Garnet”፣ “Red Agates”፣ “Green Agate”፣ “white Agate”፣ “Blue Agate”፣ “Banded Agate”፣ “black and green Tourmaline” እና “Amazonite” በቁጫና ቦረዳ ወረዳዎች የድንጋይ ከሰል፣ በኮንሶ ዞን  “Basaltic and Granitic rocks”፣ “Asbestos”፣ “Apatite”፣ “Emerald” እና “Tourmaline” በደቡብ ኦሞ ዞን “Dimension Mineral (Granite) Corundum” እና “Marble” እንዲሁም በቡርጂ ዞን “Bentonite”፣ “Chalcedony”፣ “Ruby and Sapphire” የተሰኙ የጌጣጌጥ፣ ለኢንደስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ክምችት መኖሩ መታወቁን ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ክምችቱ በተገኘባቸው አንዳንድ ቦታዎች ባለሀብቶችና በአነስተኛና ጥቃቅን ማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች ማዕድናቱን ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ቶሌራ ሴራሚክና ለመስተዋት/ብርጭቆ  ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውሉ “Bentonite”፣ “Quantize” እና “Feldspar” የተሰኙ ማዕድናት በጋሞና ቡርጂ አካባቢዎች በስፋት የሚገኙ በመሆኑ አርባ ምንጭ ላይ የሴራሚክና መስተዋት ፋብሪካ ቢከፈት አዋጭ በመሆኑ ባለሀብቶች በመስኩ ቢሠማሩ ራሳቸውንም ሆነ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በነዚህ አጭርና ውስን ቦታዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ሀገራችን ያልተነካ የማዕደን ሀብት ያላት መሆኑን ያረጋገጡ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ቶሌራ ይህንን ሀብት በስፋት አጥንቶ ጥቅም ላይ ማዋል የማኅበረሰቡንና የሀገሪቱን ልማትና ብልጽግና በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ ይረዳልም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት