Print

አርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት ጋር በመተባበር “አርባ ምንጭ ታንብብ!” በሚል መሪ ቃል ታላቅ የንባብ ሳምንት አዘጋጅቷል፡፡ የንባብ ሳምንቱ በአርባ ምንጭ ከተማ ከጥር 18-21/2016 ዓ/ም ማለትም ከፊታችን ዓርብ እስከ ማክሰኞ ድረስ ድግሱ ለአራት ቀናት ይቆያል፤ ድንቅ መርሃ ግብሮች ተካተውበታል፡፡

ቅዳሜ ጠዋት! ሁለት ሠዓት! የመጽሐፍት ዓውደ-ርዕይና ሽያጭ በታላቁ የጋሞ አደባባይ ላይ ይነግሳል፡፡

ወላጆች ለልጆቻቸው ነገ ይጠበባሉ፤ መጽሐፍትን በታላቅ ቅናሽ ይሸምታሉ፡፡ በሀገራችን አሉ የተባሉ የመጽሐፍት አታሚዎች፣ አከፋፋዮችና ሻጮች ልዩ ልዩ መጽሐፍትን በታላቅ ቅናሽ ያቀርባሉ፤ ይሸጣሉ፡፡ ትምህርት ቤቶችና ቤተ-መጽሐፍት የመደርደሪያቸውን ዕርቃን በብርቅ መጽሐፍት ይሸልማሉ፤ ይገዛሉ፡፡ ሲቀላ፣ በመጽሐፍት ቀለምና መስመር ይደምቃል፣ ዕውቀት ለገበያ ቀርቧል፡፡ ቅዳሜ ጠዋት! ጋሞ አደባባይ፡፡ ይጎብኙ፤ ይሸምቱ፤ ያንብቡ፡፡

ቅዳሜ ከሰዓት! አሥር ሰዓት! የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን ከዕውቅ ደራሲያን ጋር በጥበብ ሰረገላ ይሳፈራሉ፤ ፀሐፍት ሥራቸውን ለታዳሚያን ያቀርባሉ፡፡ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ እና ሌሎችም የሚገኙበት የጥበብ ድግስ ሲሆን የእውነት እና ዕውቀት ጥልቀት በግጥም ይበረበራል፤ ቀልብ ይመለሳል፤ ልቦና ይርሳል፡፡ ታላላቅ ደራሲያን የልቦለድ ሥራቸውን ያቀርባሉ፤  ወግ እና መነባንብን ያስከትላሉ፡፡ ታዳጊ ፀሐፊዎች ሥራቸውን ያቀርባሉ፤ ለሽልማት ይወዳደራሉ፡፡  የጥበብ ጣር ጩኸት ይሰማል፤ ቅዳሜ አሥር ሰዓት ላይ በጋሞ ባህል አዳራሽ የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን የማይቀሩበት ቀጠሮ ተይዟል፡፡

ይምጡ! ይታደሙ! ይሳተፉ፡፡ መግቢያው ተከፍሏል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት