Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Hope of Light›› ከተሰኘ ሀገር በቀል ግብረ ሠናይ ድርጅት እና በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በሆስፒታሉ ተቋርጦ የነበረውን የማኅፀን ፊስቱላ ሕክምና መጋቢት 3/2016 ዓ/ም ዳግም ሥራ አስጀምሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅፀንና ፅንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የማኅፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር መኮንን መንግሥቱ በሦስቱ ተቋማት መካከል ከተደረሰው ስምምነት በኋላ የተለያዩ የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለሁለት ታካሚዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና በማድረግ ሥራው በሆስፒታሉ ዳግም ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቀዶ ጥገና ሕክምናው የ‹‹Hope of Light›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የዘርፉ ስፔሻሊስት በሆኑት ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የሚመራ ሲሆን በቀጣይ ከሚሰጡ ሥልጠናዎችና የተግባር ልምዶች በመነሳት ሕክምናው በዩኒቨርሲቲውና በሆስፒታሉ ባሉ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን መሆኑን ዶ/ር መኮንን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኘው ማኅበረሰብ ዘንድ በሽታውን የመለየት ሥራ እንዲሁም በሽታውን ከመከላከል አንጻር አጋዥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር መኮንን በቀጣይ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት የስፔሻሊቲ ትምህርት ፕሮግራሞችን የመክፈት ውጥን መኖሩንም አክለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አንተነህ ካሳዬ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ዓመት ተቋርጦ የቆየውን የፊስቱላ ሕክምና ዳግም ለማስጀመር ሦስቱ ተቋማት ለ10 ዓመታት የሚቆይ የመግባቢያ ስምምነት ታኅሣሥ 2016 ዓ/ም ላይ ተፈራርመው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እናቶች የማኅፀን ፊስቱላ ችግር ሲገጥማቸው ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመሄድ እንደሚገደዱና ይህም ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እንደሚዳርጋቸው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ሕክምናው በሆስፒታሉ መጀመሩ ይህን የማኅበረሰቡን እንግልት እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል፡፡

የሕክምናው አገልግሎትም የታካሚዎችን የሕክምና፣ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የትራንስፖርት መሉ ወጪ በመሸፈን በነፃ የሚሰጥ ሲሆን ከጋሞ ዞን ባሻገር ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ ታካሚዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚእንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት