Print

አርባ ምንጭ የዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮምሽን ጋር በመተባበር በሽግግር ፍትሕ ሂደት ዙሪያ ወጣቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ሚያዝያ 15/2016 ዓ/ም ገለጻ አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት የሽግግር  ፍትሕ የወንጀል ሕግ ክፍል ሲሆን ተቀዳሚ ግቡ ጉልበት ያለው አካል በሚፈጽመው ግጭትና ጦርነት ምክንያት የሚፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከላከልና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ በማድረግና ዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሀገር መፍጠር ነው፡፡  የሽግግር ፍትሕ አንድን ሀገር ከግጭት ወደሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረግ ሽግግር መሆኑን የጠቆሙት ም/ፕሬዝደንቱ  ጽንሰ ሃሳብን አስቀድሞ ለባለ ሙያዎች እንዲሁም ለብዙኃኑ ሕዝብ ለማስረዳትና ግንዛቤ ለመፍጠር ይህን መሰል ፎረም ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

 የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር ዳኛቸው ወርቁ የፕሮግራሙን ዓላማ አስመልክተው እንደገለጹት በሀገሪቱ ዋና የፖሊሲ ትኩረት በሆነው በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ  ለተማሪዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ማኅበረሰብ የንቃተ ሕግ ግንዛቤ መስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮምሽን (UNOHCHR) የምስራቅ አፍሪካ ክልል ቢሮ የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሚስ ፌዴሪካ ሲማንዲ /MS Fedrica Seymandi/ የሽግግር ፍትሕ መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳብና መርሆዎቹን አስመልክቶ ባደረጉት ገለጻ የሽግግር ፍትሕ በግጭት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ከግጭት ወጥተው የሰብአዊ መብትን እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚጠቀሙበት ዋነኛ የፖሊሲ መሳሪያ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ተቀባይነት እንዲኖረው እውነትን ማፈላለግና ማውጣት፣ ወንጀል ፈጻሚዎች ኃላፊነት እንዲወሰወዱ ማድረግ፣ ተጎጂዎች ከተለዩ በኋላ በቂ የሆነ ካሳ ወይም ለጉዳታቸው ዕውቅና መስጠት እንዲሁም ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ ዋና ዋና መርሆዎቹ እና የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማርቀቅና የማውጣት ሂደት ክንውን የሚሉት በፕሮግራሙ ትኩረት ከተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት