የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ‹‹በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ42ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ በ1ኛ ሴሚስተር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ሚያዝያ 22/2010 ዓ.ም የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሽልማት ፕሮግራሙ ሴቶች በየትኛውም የትምህርትም ሆነ የሥራ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤት ማምጣት ይችላሉ የሚለውን ሀሳብ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሥርዓተ-ጾታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ‹‹ከእያንዳንዱ ጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች›› የሚለው አባባል በሀቅ ላይ የተመሰረተና ሴቶች ምን ያህል ተጽእኖ መፍጠር እንደሚችሉ የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡ ሴት ተማሪዎችም ‹‹ሴት ልጅ አትችልም›› የሚለውን ኋላ ቀር አባባል በሥራቸው ቀይረው ከወንዶች እኩል ተፎካካሪና ውጤታማ መሆን እንዲሁም መልካም ስምና ዝና ማትረፍ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች 36 በመቶው ሴቶች ናቸው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ይህም በተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም መምህራን በተለይ ዝቅተኛ ውጤት ላላቸውና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ሴት ተማሪዎችን በብዛት ለማፍራት በእጅጉ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሄዋን ደምሴ በበኩላቸው ሴቶች ለተሰማሩበት ሥራ ትኩረት ከሰጡ የሚደርሱባቸውን ተጽዕኖዎች ተጋፍጠውና ጥሩ የሥራና የአመራር ክህሎት ኖሯቸው ማንኛውንም ሥራ ከወንዶች እኩል ማከናወን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሴት ተማሪዎች ለራሳቸው ክብር መስጠትና የእችላለሁ መንፈስ መላበስ  ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በእለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ተሞክሮ እና የሴቶችን ውጤታማነትና ከወንዶች እኩል ችሎታና አቅም እንዳላቸው የሚገልጹ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡

ፕሮግራሙን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሴት ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ታድመዋል፡፡