ለዩኒቨርሲቲው የ2010 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች የቅድመ-ምረቃ ምሽት ፕሮግራም ሰኔ 19/2010 ዓ/ም በዋናው ግቢ ስታዲዬም በድምቀት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በፕሮግራሙ መክፈቻ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ተማሪዎች በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚገጥሟቸውን ማናቸውንም ውጣ ውረዶች በመቋቋም በስኬት አጠናቀው ለዚህ ቀን በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው በሚወጡበት ወቅትም ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋም ሀገሪቱ በምትፈልገው መጠን ያገኙትን እውቀትና ልምድ በታላቅ ተነሳሽነት በመፈፀም ለማህበረሰቡና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት የበኩላቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ መጪው ጊዜ ለሀገሪቱ የብሩህ ተሰፋ ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንትና ተማራቂ ተማሪ ደምሰው ፈረደ በበኩሉ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሲፈጽሙ የነበሩትን ሰናይ ተግባራት በገሃዱ ዓለምም በመተግበር ሙያዊ ስነ-ምግባር ተላብሰው ባላቸው እውቀት ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ማህበረሰቡን ብሎም ሀገሪቱን በሚፈለገው ደረጃ እንዲያገለግሉና ወደ ሚፈለገው የእድገት ማማ በማድረስ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ አስገንዝበዋል፡፡

የእግር ኳስ ግጥሚያ፣ አርቲስት ሳንቾ (አታሳዩኝ ከሷ ሌላ) ከአዲስ አበባ በመጡ ዲጄዎች አጃቢነት ያቀረበው ጣዕመ ዜማ እና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የዘመናዊና ባህላዊ ውዝዋዜ ቡድን ለፕሮግራሙ ድምቀት ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የኮሌጅና የፋከልቲ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከአምስቱ ካምፓሶች የመጡ የ2010 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች እና ሌሎችም እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን ለበዓሉ ስኬት አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡