በግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የእፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ችግሮቹ ላይ ትኩረት ያደረጉ 12 በተግባር የተደገፉ የምርምር ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡

ተማሪዎቹ የተለያዩ የምርምር ዘዴዎችን በመጠቀም በበቆሎ፣ በአኩሪ አተርና ሰሊጥ ሰብሎች ላይ ምርምሮችን በማድረግ ምርታማ ለመሆን የሚረዱ የግብርና ዘዴዎችን በተግባር  መለየት ችለዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ቱማ አየለ ተማሪዎች የምርምር ሥራዎችን መሥራታቸው በክፍል ውስጥ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር እንዲፈትሹ በማድረግ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡ በተማሪዎቹ ምርምር የተገኙትን አዳዲስ ግኝቶች በማሳደግና በማስፋት ለአርሶ አደሩ ለማስተላለፍ ኮሌጁ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የእፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ተወካይ መ/ር መሠረት ቱርኮ እንደተናገሩት ተማሪዎች ይህን መሰል በተግባር የተደገፈ ምርምር በጋራ ማከናወናቸው እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ የተሻለ የምርምር አቅም እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል፡፡

የትምርት ክፍሉ የ3ኛ ዓመት ተማሪ አስካለች በቀለ በአኩሪ አተር ምርታማነት ላይ በሠሩት በተግባር የተደገፈ ጥናትና ግኝት ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸውን ገልፃ በምርምሩ ለወደፊት ሥራቸው አጋዥና ጠቃሚ ልምዶችን ማግኘት መቻሏን ተናግራለች፡፡

ሌላው የትምህርት ክፍሉ ተመራቂ ተማሪ በለጠ አከለ እንደገለፀው በሠሩት የምርምር ሥራ ውጤታማ የአስተራረስ፣ የአዘራር እንዲሁም አዳዲስ ሰብሎችን የማላመድ ዘዴዎችን በተግባር መለየት መቻላቸውን ገልጿል፡፡ ወደ ሥራ ሲሰማሩም አርሶ አደሩ እነዚህን ዘዴዎች እንዲጠቀም በማድረግ ምርታማነትን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ውሰጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ ተናግሯል ፡፡

የእፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል በዘንደሮው ዓመት በግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በሚገኙ ትምህርት ክፍሎች መካከል በተደረገው የተማሪዎች የምርመር ሥራ ውድድር ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡