የዩኒቨርሲቲው የሦስተኛውን ዙር ስትራቴጂክ ዕቅድ የሦስት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ሰኔ 11/2010 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ት/ግ/ዳ ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በቅድመ-ምረቃና በድህረ-ምረቃ(የ3ኛ ዲግሪን ጨምሮ) የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈቱ፣ ባለፉት አምስት አመታት የቅበላ አቅሙን ከአስራ አራት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ አራት (14,914) ወደ አሥራ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ሰለሳ ሁለት (18,132) ከፍ ማድረግ መቻሉ እና የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ  በመማር ማስተማር በኩል ጠንካራ ጎኖች ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የትምህርት ፍትሀዊነት መሻሻልን በተመለከተ ትምህርታዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የማንበቢያ ክፍሎች እጥረት እንዳይፈጠር በመጣር፣ የስርዓተ-ፆታ ፖሊሲዎችንና የማስፈፀሚያ ስልቶችን በማጠናከር ወደ ዩኒቨርስቲው የሚመጡ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመምህራን የምርምር ተሳትፎ የሙሉ ጊዜ ተመራማሪዎችን ቁጥር 25 ማድረስ ተችሏል፡፡ በታዋቂ ጆርናሎች ላይ የሚታተሙ የምርምር ውጤቶችን 164 እና የችግር ፈቺ ምርምሮች ቁጥር 636 ማድረስ ተችሏል፡፡ የምርምር ውጤቶችን ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ለማህበረሰቡ ለማሸጋገር በ2010 ዓ/ም በቁጥር 12 ከነበረበት  ወደ 19 ማሳደግ ተችሏል፡፡ የሴት መምህራን ተሳትፎ በ2007 ዓ.ም 9.3% ሲሆን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጋማሽ በ2010 ወደ 11% ደርሷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በታለመው መሰረት ለማሳካት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡

የትምህርት አማካሪዎች ለተማሪዎች የሚሰጡት የትምህርት ድጋፍ፣ የመምራትና የማማከር አገልግሎቶች በቂ አለመሆን፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በቂ አለመሆን፣ የሴት ተማሪዎችና ሌሎች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች መጠነ- ማቋረጥና መጠነ-መውደቅ (ብክነት) ምጣኔ መሻሻል ቢኖርም የተፈለገው ደረጃ አለመድረስ እንደ ድክመት የተስተዋሉ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የመምህራንን ቁጥር ከመጨመር፣ የትምህርት ደረጃን ከማሳደግና የማስተማር ክህሎትን ከማዳበር ጎን ለጎን የበቁ መምህራንን ለመሳብና ለማቆየት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት መምህራን በጥናትና ምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ላይ ተሠማርተው ለህብረተሰቡ ማበርከት የሚገባቸውን አስጸዋኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት ይሠራል፡፡