የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ ከሰውኛ ኢንተርቴይመንት ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር ‹‹አድዋ የሰውነት ማኅተም›› በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውን 123ኛውን የአድዋ ድል በዓል ከየካቲት 16-23/2011 ዓ/ም በደመቀ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአድዋ ድል በዓልን ከአጋሮቹ ጋር ማክበሩ በምሁራን መካከል ታሪክን መሠረት ያደረገ የእውቀት ሽግግር ከማድረጉም ባሻገር ከሰውኛ ኢንተርቴይመንት ፕሮዳክሽን ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያደረገው ስምምነት አካል ነው፡፡

‹‹የአድዋ ድል አስተዋፅዖ›› በተሰኘ የታሪክ ጽሑፍ ዙሪያ ገለፃ የሰጡት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መ/ር አቶ እውነቱ በላቸው የአድዋ ድል የዘር እና የኃይማኖት ክፍፍል ሳይሆን የአንድነትና የመተባበር መንፈስ የታየበት እንዲሁም ድሉ የኢትዮጵያ ብሎም በመላው ዓለም የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት መንፈስ የታየበት የጥቁሮች ሁሉ ኩራት ነው ብለዋል፡፡ ድሉ የአሁኑ ትውልድ በራሱ እንዲተማመን እና ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በመተባበር መንፈስ ለአገራዊ አንድነቱ የበኩሉን እንዲወጣ ጥልቅ መልዕክት ያለው መሆኑን መ/ር እውነቱ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ በአድዋ ጦር ሜዳ››፣ ‹‹የአድዋ ድል እና ኢትዮጵያዊነት››፣ ‹‹የአድዋ ድል አስተዋፅዖ›› እንዲሁም ‹‹የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና  ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ የመረጃ አደረጃጀት ከአድዋ ድል አንፃር›› የተሰኙ ጽሑፎች በምሁራኑ ገለፃ ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ እንደተገለፀው ነጮች በጥቁር ህዝቦች ላይ ያላቸው የንቀት አመለካከት እንዲሁም የኢንደስትሪ አብዮቱ የፈጠረው የአውሮፓውያን ባለሀብቶች የኢትዮጵያን ሀብት የመቀራመት ጉጉት ለአድዋ ጦርነት መጀመር መነሻ ምክንያቶች ከነበሩት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ድል እንደሆነ አምኖ አለመቀበል፣ የተዛባ አመለካከት፣ የተሳሳተ አተረጓጎም እንዲሁም ታሪክን መሠረት ያደረገ በቂ እውቀት አለመኖር የአድዋ ድል መታሰቢያ በተጠናከረ መልኩ በሁሉም ቦታ እንዳይከበር ከሚያደርጉ ምክንያቶች ጥቂቶቹ መሆናቸው በፓናል ውይይቱ ከተነሱ አስተያየቶች መካከል ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተሳታፊዎች ዩኒቨርሲቲው መሠል ዝግጅቶችን በማዘጋጀትና ተሳታፊ በመሆን የአገር ታሪክ ግንዛቤ ሊያሳድግ የሚያስችል የእውቀት ሽግግር ዙሪያ የተሻለ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የምሁራን ጉባኤ፣ የኪነ-ጥበብ ምሽት፣ የባዶ እግር ጉዞ፣ የፓናል ውይይት እንዲሁም የግብር ማብላት ሥነ-ሥርዓት የፕሮግራሙ አካል ሲሆኑ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተመራው የደራሼ የባህል ኪነት ቡድንም ባህላዊ ትዕይንቶችን በማሳየት በዓሉን አድምቋል፡፡