አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ Lucy Consulting Engineers PLC (LUCY) ከተሰኘ ድርጅት ጋር በonline ትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መጋቢት 4/2011 ዓ/ም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ስምምነቱ ምርምርና ማማከር፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ክለሳ፣ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮግራሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ፣ የዩኒቨርሲቲውን ትምህርቶች ለዓለም- አቀፍ ተማሪዎች በኦንላይን መስጠት፣ ተቋሙን ከተለያዩ የውስጥና የውጪ የሙያ ማኅበራት ጋር በትብብር እንዲሠራ ማድረግ፣ የተላመዱ ቴክኖሎጂዎችን ማሸጋገርን ያካትታል ብለዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ እንደተናገሩት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና በE-learning የታገዘ ትምህርት ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ስምምነቱ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ ነው፡፡

የLucy Consulting Engineers PLC (LUCY) ፕሬዝደንት ዶ/ር ሐብታሙ መለሰ በበኩላቸው ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተመራጭ እንዲሆን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡

ድርጅታቸው በአሜሪካ አገር የE-learning platform ሰርቨር እንዳለው የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ይህም ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ፕሮግራሞቹን ዲጂታላይዝ በማድረግ በቀላሉ በonline በመስጠት ዓለም-አቀፍ ተማሪዎችን እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል፡፡ በውኃው ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ያሉት ፕሮግራሞችና ሌሎች ለE-learning አመቺ የሆኑ የትምህርት መስኮች በonline ለመስጠት እንደታቀደ የተናገሩት ዶ/ር ሐብታሙ ፕሮግራሞቹ የሚሰጡት በዩኒቨርሲቲው መምህራን በመሆኑ መምህራኑም ጭምር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለመማር የግድ አርባ ምንጭ መምጣት አይጠበቅም ያሉት ዶ/ር ሐብታሙ በየትኛውም የዓለማችን ቦታ የሚገኝ ሰው ጊዜና ቦታ ሳይገድበው በዩኒቨርሲቲው መማር እንዲችል ሁለቱ ተቋማት በጋራ ይሠራሉ ብለዋል ፡፡ ወደ ሥራ ለመግባትና ዓለም-አቀፍ ተማሪዎችን ለማግኘት ዩኒቨርሲቲው የማርኬቲንግና የፕሮሞሽን ሥራ በስፋት መሥራት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተከታታይና ርቀት መርሃ-ግብሮች በርካታ ተማሪዎች እንዳሉት የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም በተለይ ለርቀት ትምህርት ኮርሶች ሞጁል ዝግጅት፣ ህትመትና ስርጭት ከፍተኛ ወጪ ያወጣል፡፡ ይህንን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት በስምምነቱ መሰረት የማስተማሪያ ሞጁሎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ተማሪዎቹ ኮርሶቹን online ማግኘት እንዲችሉ ይደረጋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት