ዩኒቨርሲቲው ኢንተርን የህክምና ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች እና በህክምና ሙያ በሚገጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ሚያዝያ 17/2011 ዓ/ም ከ 150 የ6ኛ ዓመት ኢንተርን የህክምና ተማሪዎች ጋር ተወያይቷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ እንደተናገሩት ተማሪዎች በነፃነት የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለአገር አስፈላጊ በመሆኑ በተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዩኒቨርሲቲው በፌዴራል ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር የሚኖረውን ሙያዊ ግንኙነት  በማሻሻልና በማጠናከር ለጤናው ሁለንተናዊ ተሳትፎ የበኩሉን ይወጣልም ብለዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ጥያቄዎችን ሠላማዊ በሆነ መልኩ መጠየቅ ከሰለጠነ ማኅበረሰብ የሚጠበቅና ለሌሎች አርአያ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች የሚያቀርቧቸው ማናቸውም ጥያቄዎች መረጃን መሠረት ያደረጉ ሊሆን እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ር ታምሩ ውይይቱ ኢንተርን የህክምና ተማሪዎች በሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የ6ኛ ዓመት ኢንተርን የህክምና ተማሪ ዶ/ር ፍቅሩ ደመቀ እንደተናገረው ጥያቄያቸው ለዩኒቨርሲቲው ሳይሆን በዋናነት ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ነው፡፡ የተማሪዎቹ መሠረታዊ ጥያቄ የጅማና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርን የህክምና ተማሪዎች ያቀረቡትን የመብትና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ለመጋራት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጤና ሥርዓት እንዲሻሻል ለማድረግ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ጥያቄያቸው የአገሪቱ የጤና ሁኔታ እነርሱንም የሚያሳስብ በመሆኑ፣ ሊከፈላቸው ስለሚገባ ጥቅም እና በሙያቸው ስለሚሰጣቸው ክብር እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አለመሆኑን የገለፁት ተማሪዎቹ ሚዲያው ዝምታውን በመስበር የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለህዝቡና ለመንግሥት ተደራሽ በማድረግ ጉዳዩ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በህክምና ሥራችን በሚኖረን የ36 ሰዓት ያለእረፍት ቆይታ የሰው ልጅ እንደሚሠራው ስህተት በሥራችን ላይ ክፍተቶች ቢፈጠሩ አግባብ ባለው መልኩ ልንጠየቅ ይገባል ያሉት ተማሪዎቹ በሽተኛ ሲሞት ሐኪሙን መውቀስ በሽተኛው ሲድን ተቋሙን የሚመራውን አካል ማወደስ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ አክለው እንደተናገሩት ‹‹ከነጭ ጋውን ለባሽ ይሻላል ነጭ ሽንኩርት›› የሚሉና መሰል የተሳሳቱና የሙያውን ክብር ጥላሸት የሚቀቡ አባባሎችና ወሬዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ መልቀቅ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ በዚህ ተግባር የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

የህክምና ዶክተሮች፣ የነርሶች እና የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሙያን መሠረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል አለመኖር፣ የደኅንነት ክፍሉ መላላት፣ የኢንተርን ዶክተሮች በቂ የማረፊያ ክፍል አለመኖር እንዲሁም የሆስፒታሉን ደረጃ ሊገልፁ የሚችሉ  ግብዓቶች ተሟልተው አለመገኘት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወቅታዊ አቋም የሚያሳዩና መሻሻል የሚገባቸው  ክፍተቶች ብለው የህክምና ተማሪዎቹ ከገለጿቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

እንደ ህክምና ተማሪዎቹ ገለፃ ኢትዮጵያ ‹‹እናት ለምን ትሙት›› የተሰኘና ሌሎችም ጥሩ መርሆዎችን በጤና ፖሊሲ ያካተተች ቢሆንም አገሪቱ ላይ ያለው የጤና ሥርዓት ለባለሙያው ጥቅም ያልቆመና የዘርፉን ምሁራን የሚያሳጣ በመሆኑ፣ በጤናው ዘርፍ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ተቋሙ የሚመራው ከሙያው ውጭ በሆኑ የፖለቲካ አመራሮች በመሆኑ እንዲሁም ለጤና  ባለሙያዎች የሚሰጠው ክብርና ጥቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ፖሊሲው በትክክል እንዳይተገበርና የአገሪቱ የጤና ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡

ተማሪዎቹ ለሙያው የሚሰጠው ክብርና ለባለሙያው የሚገባው ጥቅምና መሠል ጥያቄዎች እስኪመለሱ ድረስ ቅሬታቸውን  በሰላማዊ  መንገድ ማቅረብ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት