ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን (livestock production) በዘመናዊ መልኩ ለማጎልበት እንዲቻል ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ኮሌጁ በእንስሳት ምርምር ዙሪያ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የመጡ የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ልምዳቸውን በማካፈል የእውቀት ሽግግርን ለመፍጠር በማለም ግንቦት 03/2011 ዓ.ም ዓለም አቀፍ አውደ-ጥናት አካሂዷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በዕለቱ 4 ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ህንድ እና ቤልጅየም የተወጣጡ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡ ምሁራኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ200 በላይ የምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዳሳተሙም ተጠቅሷል፡፡ ጥናቶቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ133 አገራትን ተሞክሮ የሚዳስሱ ሲሆን በተለይ በእንስሳት ምጣኔ ሀብትና ትንተና ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የእንስሳት እርባታ፣ ለእንስሳት እርባታ የሚያስፈልጉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች እንዲሁም የእንስሳት አመጋገብና አያያዝ በጥናቱ የተዳሰሱ ነጥቦች ናቸው፡፡

የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሀቅ ከቸሮ እንደገለጹት ጥናቶቹ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ለማስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ ስለሚኖራቸው ተገምግመውና ተመዝነው የማኅበረሰቡን ችግር እንደሚፈቱ የታመነባቸው በመሆኑ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ ይደረጋል፡፡

ምርምር የመጨረሻ ግቡ ወደ ማኅበረሰቡ ወርዶ ችግሮችን መፍታት ነው ያሉት ዲኑ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የህብረተሰቡን ችግር በመለየት የማኅበረሰቡን ህይወት ሊቀይሩ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተወሰነ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ምርምሮችን በማካሄድ በቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

መሰል ውይይት በየጊዜው መዘጋጀቱ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የአተገባበር ስልቶችን በማፋጠን አገሪቱ እያንቀሳቀሰች ያለችውን  የዘርፉን ኢኮኖሚ ሊያነቃቃው እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ ህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ እና ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ መምህራን፣ በግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ከአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል የመጡ ተሳታፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዓውደ ጥናቱ ታድመዋል፡፡