የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከሁሉም ካምፓሶች ለተወጣጡ ተማሪዎች ከሚያዝያ 11-13/2011 ዓ.ም የኤች አይ ቪ እና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ሜይንስትሪሚንግ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለፁት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ጉዳይ የሰው ልጆች ሁሉ ችግር በመሆኑ ተማሪዎች ባሉባቸው ክበባት ሁሉ የኤች አይ ቪ ጉዳይን እንደ ዋና ተግባር አድርገው እንዲሠሩ ለማድረግ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በስልጠናው ሰነድ እንደተብራራው የህይወት ከህሎት ሰዎች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ፍላጎታቸውን ለማሟላትና ፈተናዎችን ለመወጣት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም፣ ብቃት እና ችሎታ እንዲሁም ጤናማ ህይወት ለመኖር የሚያስችል የግል ጥበብ ነው፡፡

የህይወት ክህሎት ትምህርት ዓላማ በመረጃ፣ በዕውቀትና በክህሎት ላይ መሠረት አድርጎ የመወሰን ብቃት እንዲያዳብሩ ማድረግ፣ በህይወት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ፈተናዎችንና ለአደጋ አጋላጭ ጎጂ ባህሪያትን ለይተው በማወቅ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ማስጨበጥና ወጣቶች ራሳቸውን ከኤች አይቪ/ኤድስ ለመከላከል እንዲችሉ በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው፡፡

ከአ/ምንጭ ብርሃን ፀረ-ኤድስ ማኅበር የመጡት አሰልጣኝ  አያሌው ሰብስቤ በበኩላቸው ወጣቶች ከዕድሜያቸው ጋር ተያይዞ በሚመጡ በርካታ አካላዊና የስሜት ለውጦች ሳቢያ የሚከሰቱ ተፅእኖዎችን ተቋቁመው እንዲያልፉ የሚያስችሉ ጉዳዮች የሥልጠናው አብይ ትኩረት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኝ ተማሪ መቅድም ግርማና ተማሪ ምስራቅ በዛብህ በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ለወደፊት ሕይወታቸው ጠቃሚ የሕይወት ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረው ሥልጠናው ከተማሪው ባለፈ ለሠራተኞችም ቢሰጥ መልካም ነው ብለዋል፡፡