በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል በ ‹‹Condensed Matter Physics››፣ ‹‹Quantum Optics & Information››፣ ‹‹Astrophysics›› እና ‹‹Laser Spectroscopy and physics Education›› የፊዚክስ sub-specialization መስኮች የ2ኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር ግንቦት 17/2011 ዓ/ም የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በፕሮግራሙ ላይ የመክፍቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ አገራዊ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞች የማስፋፋት ተልዕኮ እንደተሰጠው አስታውሰው የፕሮግራሞቹ መከፈትም ከዩኒቨርሲቲው ዕቅድ አንፃር ሲታይ አንድምታው ጉልህ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው አቻ ክፍሎች ጋር ሲነፃፃር የተሻለ ቤተ-ሙከራ እንዳለው የተናገሩት ዶ/ር የቻለ የጎደሉ የቤተ-ሙከራም ሆነ የቤተ-መፃህፍት ግብዓቶችን ለማሟላት ዩኒቨርሲቲው ቁርጠኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ እንደተናገሩት የሚከፈቱት የትምህርት መስኮች በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቁመው በተለይ በአስትሮፊዚክስ መስክ አገሪቱ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች በምትገኝበት በዚህ ወቅት የፕሮግራሙ መከፈት በመስኩ እንደ አገር ያለውን የሙያተኞች ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል፡፡ ፕሮግራሞቹን በቀጣይ ዓመት ለማስጀመር ኮሌጁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ አንጁሎ በበኩላቸው ጊዜው የሣይንስና ቴክኖሎጂ በመሆኑና ፊዚክስ ደግሞ በአገሪቱ የሣይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወት ዘርፍ በመሆኑ በመስኩ የሰለጠኑ ምሁራንን ማፍራትን ዓላማ በማድረግ ፕሮግራሞቹን ለመክፈትና ሥርዓተ-ትምህርቱን ለማዘጋጀት ትምህርት ክፍሉ እንደተነሳሳ ገልፀዋል፡፡ ሥርዓተ-ትምህርቱ ከመዘጋጀቱ በፊት በመስኮቹ ተፈላጊነት ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ያስታወሱት አቶ ወንድማገኝ ከዚህ ቀደም የውስጥ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ መደረጉንና በቀጣይም ሥርዓተ-ትምህርቶቹ በዩኒቨርሲቲው ሴኔትና ቦርድ ከፀደቁ በኋላ በ2012 የትምህርት ዘመን የማስተማር ሥራ ይጀመራል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት