በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ‹‹ በፊዚክስ ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ›› የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም መክፈት ያስችለው ዘንድ ሰኔ 7/2011 ዓ/ም የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ አካሂዷል፡፡

የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ አንጁሎ በዩኒቨርሲቲው የፊዚክስ ኮርስ በ1979 መሰጠት እንደተጀመረና ትምህርት ክፍሉ በ1996 ራሱን ችሎ እንደተመሠረተ አስተውሰው አሁን ላይ ትምህርት ክፍሉ በአንድ የመጀመሪያና በሁለት የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው፡፡ ትምህርት ክፍሉ በ5 sub-speciality የትምህርት መስኮች የማስተርስ ፕግራሞችን በቀጣይ ዓመት ለመክፍት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትልና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሴ ታደገ በበኩላቸው ይህን መሰል ለተግባር ትምህርት መስፋፋት የሚያግዙ የትምህርት ፕሮግራሞች መከፈታቸው ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው ትምህርት ክፍሉም ሆነ ኮሌጁ መሟላት ያለባቸውን ግብዓቶች በማሟላት እንዲሁም ያሉትን ግብዓቶች በአግባቡ በመጠቀም ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ እንደገለፁት ለጥሩ የመማር ማስተማር ሂደት በተለይ እንደ ፊዚክስ ያሉ ትምህርቶች  ከክፍል ውስጥ ማስተማር ባሻገር በቤተ-ሙከራ ውስጥ በተግባር ሊደገፉ ይገባል፡፡ አሁን ላይ በኮሌጁ የሚከፍተው ፕሮግራምም በመስኩ እንደ አገር ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል፡፡ ት/ክፍሉ ፕሮግራሙን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ የሰው ኃይል እንዳለው የተናገሩት ዶ/ር ፈቃዱ የጎደሉ የቤተ-ሙከራ ግብዓቶች እንዲሟሉ ኮሌጁ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

በሥርዓተ-ትምህርት ግምገማው ወቅት እንደተገለፀው በመስኩ የሚመረቁ ተማሪዎች በትምህርት፣ በምርምርና በታዳሽ ኃይል ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ ኢንደስትሪዎች ውስጥ ተፈላጊ መሆናቸው በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት