ዩኒቨርሲቲው 16 ሚሊየን ብር በሚሆን ወጪ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ለከተማው ውኃ አገልግሎት ድርጅት ያስረከበ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገልግሎት አቅርቦትና አጠቃቀም የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለከተማው ህብረተሰብ የሚቀርበውን የውኃ አገልግሎት በጋራ ሲጠቀም የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው ተጨማሪ አራት ካምፓሶች በመገንባታቸውና የተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በተፈለገው መጠን አቅርቦትንና ፍላጎትን ማጣጣም አልተቻለም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና በተጓዳኝም የከተማውን ነባር የውኃ አቅርቦት አቅም ለማሳደግ በ2006 ዓ.ም ተጨማሪ የውኃ ፓምፕ ተከላና የመስመር ዝርጋታ ስራ አከናውኗል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ውኃ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ አብርሃም እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በሰከንድ 60 ሜትር ኪዩብ የነበረውን የውኃ አቅርቦት ወደ 94 ሜትር ኪዩብ አሳድጓል፡፡ በመሆኑም በቀን 3 ሚሊየን ሊትር ተጨማሪ  ውኃ ወደ ነባሩ የውኃ ቋት በማስገባት የከተማውን የውኃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ አቃሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በውኃው መስክ ቀዳሚ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ለአካባቢው ህብረተሰብ ተደራሽ ሥራዎችን በማከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የከተማው ነዋሪዎችንና የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ካልሆነ በቀር የውሃ መቋረጥ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚያደርግ ነው፡፡
በከተማው ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች በዘላቂና አስተማማኝ ደረጃ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያገኙበት ሥርዓት እና ከአቅርቦቱ ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲገጥሙ በቅንጅት መፍትሔ የሚሰጥበት አሠራር በጋራ መግባቢያ ሰነዱ ተካቷል፡፡ 
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት