ምርምር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስቀመጧቸው የትኩረት መስኮች አንዱና መሰረታዊ እንደመሆኑ መጠን ተቋሙንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም በገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የሚያስችል ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ በሚሰጣቸው አራት የምርምር መርሆዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን መጠበቅ፣ ለማህበረሰብ ጠቀሜታ ያለው መሆን፣ ለላቀ ምርምር ክፍት መሆን እና ለተመራማሪዎችና ለመምህራን የተመቻቸ የምርምር አካባቢዎችን መፍጠርን  ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡
የምርምር መርህን መተግበር በዋናነት ጥናትና ምርምሮች እንዲጎለብቱና በዘላቂነት ተጨባጭ ውጤት እንዲያበረክቱ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር አስተባባሪ አቶ ዋንዛሁን ጎዳና የምርምር ንድፈ ሀሳቦች በምርምር ስነ-ምግባር ገምጋሚ አባላት ተገምግመው ሲፀድቁ ብቻ ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል፡፡
በኮሌጁ የሚካሄዱ ጥናቶች የምርምር መርህን፣ ሥርዓት እና ደንብን የተከተሉ በተለይም የሰው ልጅን ጤናና ክብር የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል  ከጥቅምት 8 - 12 /2008 ዓ.ም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የተሰጠ ሲሆን በጤናው መስክ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ጤና መሠረት ያደረጉ፣ የኮሌጁን የምርምር አቅም የሚገነቡ እና ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀትን የሚያሸጋግሩ እንዲሆኑ ታቅዶ ተዘጋጅቷል፡፡
ማንኛውም ምርምር ከመካሄዱ በፊት ሊያበረክት የሚችለው ጥቅም በጥልቅ ታይቶ የስነ-ምግባር አዎንታ ማግኘት የሚገባው ቢሆንም የምርምር ስነ-ምግባር አባላት ካለባቸው ከፍተኛ የስራ ጫና እንዲሁም የማበረታቻ ስርዓት ባለመዘርጋቱና በሌሎች ምክንያቶች የዘርፉ ሥራ ችግሮች የተስተዋሉበትና አድካሚ ነበር፡፡ ሥልጠናው የአባላቱን አቅም የሚገነባና የተሻሉ አሠራሮችን በመከተል የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው፡፡
ስልጠናው ከተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የተጋበዙ ምሁራንን፣ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ተጋባዥ መምህራንን እና ሌሎች ተመራማሪዎችን ጨምሮ ሰላሳ ሶስት ተሳታፊዎችን አካቷል፡፡ ተሳታፊዎቹ እንደገለፁት ስልጠናው መሰጠቱ በአካዳሚክ ዘርፍ በተሰማሩ መምህራንና ባለሙያዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የምርምር መርህን እንዲከተሉ ግንዛቤን የፈጠረ መሆኑንና  ዩኒቨርስቲውን  ወደ ምርምር ማዕከልነት ለማሳደግ በሚደረገው ርብርቦሽ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ኮሌጁ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የምርምር ስነ-ምግባር ኮሚቴ አባላትን አመስግኖ በማሰናበት አዲስ የሰለጠኑ አስፈፃሚዎችን በምትካቸው በመሰየም ስልጠናው ተጠናቋል፡፡