ዩኒቨርሲቲው በዘላቂ የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከዞኑ የመንግስት አካላት ጋር በትብብር የተፋሰስ ልማት፣ የተራቆተ አካባቢን መልሶ የማልማትና የተፈጥሮ ክብካቤ ሥራ በማከናውን ላይ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ጎፋ ዞን እና ከምዕራብ አባያ ወረዳ አስተዳደርና ህዝብ ጋር በመተባበር የተፈጥሮ ክብካቤና አከባቢን መልሶ የማልማት ተግባር  ከጀመረ የቆየ ሲሆን በዘርፉም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለማየሁ ታዬ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዘላቂ ልማት ለማምጣት ሲባል የማህበረሰቡን ንቅናቄ መፍጠርና ለችግኝ ማፊያ ጣቢያ የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት በዕቅዱ መሠረት የተከናወነ በመሆኑ በቀጣይነት የተዘጋጁ ችግኞችን ለአካባቢው ህዝብ ማሰራጨትና ድጋፍ  የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከተፋሰስ ልማት ሥራ በተጓዳኝ በመሬት መሸርሸርና በዝናብ እጥረት የተራቆተ አካባቢን መልሶ የማልማት ሥራ ከሚከናወንባቸው የዞኑ ወረዳዎች መካከል የምዕራብ አባያና የቦንኬ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በቦንኬ ወረዳ የሚገኘው የጉጌ ተራራ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ለማስጠበቅ በአካባቢው ካቻ ካቻሶና ጮሻ ቀበሌያት የችግኝ ማፍላት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በተመሳሳይ በምዕራብ አባያ ወረዳ የዛላ ጉትሻ ፣ ደልቦ እና ዋንኬ ዋጅፎ ቀበሌያት የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎችን በማቋቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በምዕራብ አባያ ወረዳ  ታህሳስ 5/2008 ዓ.ም  የጋሞ ጎፋ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ክብካቤ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የወረዳው አስተዳዳርና የግብርና ተፈጥሮ ክብካቤ ባለሙያዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት  የልማት ሥራዎች ከፍተኛ ባለሙያዎች በተገኙበት በዋንኬ ዋጅፎ የችግኝ ማፊያ ጣቢያ በሦስት ሄክታር ላይ የፈሉ የአካባቢውን አየር ንብረት ሊቋቋሙ የሚችሉ፣ የተለያዩ ዝርያና  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው 10,000 ችግኞች ለማህበረሰቡ እንዲሠራጩ ተደርጓል፡፡ ከተሰራጩት ችግኞች መካከል  ዝግባ፣ ወይበታ፣ ዋንዛ፣ ቡና፣ ፓፓዬ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝና  የከብቶች መኖ ሳር  ይገኙበታል፡፡
በወረዳው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ባላቸውና  የጎርፍ አደጋ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች በቀመራዬ ፕሮጀክት የተፈጥሮ ክብካቤና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች  እየተከናወኑ ሲሆን በቦረዳና በጎፋ ወረዳዎች በሚገኙ የተራቆቱ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ መልሶ የማልማትና የማቋቋም ተግባር እንደሚከናወን ታውቋል፡፡