የዩኒቨርሲቲው የሰው ሃብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት በበጀት ዓመቱ የተቋሙን የመማር ማስተማር ሥራ ለማጠናከር እና ውጤታማ የሰው ሃብት አደረጃጀትን ለማሳካት በጥናት የተደገፈ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የከፍተኛ ትምህርት ስርጭት ባልተዳረሰበት አካባቢ የትምህርት መስፋፋት ለሀገሪቱ ፈጣን ልማትና እድገት ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በ2008 የትምህርት ዘመን  የመማር ማስተማር አገልግሎቱን በማስፋፋት በጎፋ ሳውላ ከተማ ስድስተኛውን ካምፓስ በመክፈት ሥራ ጀምሯል፡፡
የዳይሬክቶሬቱ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለጹት በተቋሙ ቀደም ሲል ያሉት 5,354 የስራ መደቦች ሲሆኑ በቅርቡ የኢፌዴሪ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር ጥቅምት 22/2008 ባጸደቃቸው የተለያዩ አደረጃጀቶች  ለሳውላ ካምፓስ 562፣ ለቢዝነስና ልማት ምክትል ፕ/ጽ/ቤት፣ ለጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እና ለዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በጥቅሉ 96 እንዲሁም ለደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል 56 በድምሩ 714 አዳዲስ የሥራ መደቦች ከነባሩ ጋር በአጠቃላይ 6,068 የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የሥራ መደቦች ይገኛሉ፡፡ በአዲስ መልክ የተዋቀሩ ክፍት የሥራ መደቦችን መስፈርቱ በሚጠይቀው መመሪያ መሰረት ከወዲሁ በብቁ የሰው ሃይል የማደራጀት ሥራም እየተሰራ ነው፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በ2008 2ኛ ሩብ ዓመት ሊያከናውን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል የሠራተኞችን  የሥራ አቅም ለማጎልበት የተለያዩ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ከሌሎች አጋር የሥራ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የመስጠት እና  ክትትል የማድረግ  ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በረጅም ጊዜ ስልጠና በቴክኒክና ሙያ 147፣ በ1ኛ እና በ2ኛ ደረጃ  40፣  በመጀመሪያ ድግሪ 31፣  በሁለተኛ ድግሪ  10 እንዲሁም በ4ኛ ደረጃ የአሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ 10 በአጠቃላይ 238 የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ዳይሬክቶሬቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ተቋማዊ ዕቅድን ባማከለና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን በተከተለ መሠረታዊ የውጤት ተኮር ስርዓት የአሰራር ማዕቀፍ ለተቀመጡ ስትራቴጂያዊ ግቦች ቅድሚያ በተሰጣቸው የስራ ዘርፎች በግማሽ ዓመቱ የ132 መምህራን፣ የ63 አዳዲስ የአስተዳደር ሠራተኞች ቅጥርና የሥራ ዝውውር መፈጸሙን እንዲሁም ለ63 የአስተዳደር ሠራተኞችና 62 መምህራን የደረጃ ዕድገት እንደተሰጠ ተገልጿል፡፡
የተቋሙን የሰው ኃይል መረጃ በዳታቤዝ የማጠናከር፣  የማደራጀትና  ለተጠቃሚው የማድረስ ተግባር እየተከናወነ ሲሆን የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የስማርት ID ካርድ ዝግጅት ተጠናቆ ናሙናው ይሁንታ በማግኘቱ ቅድሚያ የተሰጠው የመምህራን መታወቂያ በመታተም ላይ ይገኛል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር እና የሰራተኛውን ግንዛቤ ከማሳደግ አኳያ በክፍሉ የአሰራር ደንብ፣ በመንግስት ወቅታዊ መመሪያዎችና የአሰራር ማእቀፎችን ዙረያ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ አከናውኗል፡፡
ዩኒቨርሲቲው  3,468  የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ 1,328  የሀገር ውስጥ  መምህራንና 111 የውጭ ሀገር መምህራንን ለመማር ማስተማር ተልዕኮ አሰማርቶ ይገኛል፡፡