የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ከተማሪዎች ህብረት እና ከሰላም ፎረም አባላት ጋር በስድስት ወራት የታዩ መልካም አፈፃጸሞች፣ ድክመቶችና ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ የዕቅድ ክንውን ውይይት የካቲት 18/2008 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ የክንውን ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ክረምቱን በዩኒቨርሲቲው ያሳለፉ 37 የቀን ተማሪዎችን በማደራጀት ልዩ አልባሳት፣ መለያና ባጅ ተዘጋጅቶላቸው ለነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል ተደርጓል፡፡ የተማሪዎች ህብረት የምርጫ ማስፈፀሚያ መመሪያን በማሻሻል የህብረቱ የ2008 ዓ/ም ምርጫ በሰላም ከመጠናቀቁም ሌላ ለተዋቀረው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለያዩ መመሪያዎችና በፋይናንስ አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያን በማሻሻል ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ለ250 ተማሪዎች በመመሪያው አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ ለመጡ በሁሉም ካምፓስ ለሚገኙ 300 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ብር 150.00 በድምሩ 45,000ሺ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአርባ ምንጭ ተሃድሶ ማዕከልን እንዲጎበኙ በማድረግ በማዕከሉ ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ዊልቸርና ክራንች ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ድጋፍ እንዲያገኙና አርቴፊሻል እግር ለሚጠቀሙ በአዲስ መልኩ ለመቀየር ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ 52 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው በየወሩ ብር 50 የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በዋናው ግቢ በሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ሪሶርስ ማዕከል የተለያዩ ሶፍትዌሮች የተጫኑባቸው 20 ኮምፒውተሮች ሙሉ በሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ ተማሪዎቹ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

በአንዳንድ የምግብ ቤት ሰራተኞች የደንብ ልብስ አጠቃቀም፣ የተማሪዎች መኝታ፣ ምግብና ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በመረጃ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የማስቻል ስራው መጓተቱ በግማሽ ዓመቱ እንደ ክፍተት የታዩ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ::

በተጨማሪም ተማሪዎች ከመኝታ አገልግሎት የተረከቧቸውን ንብረቶች በአግባቡ አለመያዝ፣ የተባረሩ ተማሪዎችን አስጠግቶ መገኘት፣ በማደሪያ ዶርሞች ውስጥ ስፖርት መስራትና የክብደት ማንሻ ማስገባት፣ ሴት ተማሪዎች የተከለከሉ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን በመኝታ ክፍሎች ውስጥ መጠቀም በውይይቱ እንደ ችግር ተነስቷል ፡፡

በመጨረሻም የምግብ፣ የመኝታ፣ የጤና፣ የጋይዳንስና ካውንስሊንግ፣ የልዩ ድጋፍ፣ የተማሪዎች አደረጃጀት እና የተማሪዎች ስነ-ምግባር በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት