ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት ግንባታ ዙሪያ ለአመራሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የካቲት 25/2008 ዓ/ም ከትምህርት ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ሰጥቷል፡፡ Pictures.

 

ስልጠናው ‹‹የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት ግንባታ ሂደት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት›› እና ‹‹የትምህርትና ስልጠና የልማታዊ መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ማስፈፀሚያ ፓኬጅ›› በሚሉ ርዕሶች ውይይት በማካሄድ ግንዛቤ ለማዳበር የተዘጋጀ ነው፡፡

የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደባልቄ ዳልጮ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕቅዳቸውን በተደራጀ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት አቅም የመተግበር ሥራዎችን ጀምረዋል፡፡ ይሁንና በለውጥ ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት ላይ ግልጽነት ባለመፈጠሩ ሥልጠናው ይህንን ክፍተት በመሙላት ወደ ተግባር ለመግባት ያስችላል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት ግንባታ ዙሪያ ተደጋጋሚ ስልጠናዎችን በመስጠት የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ለዩኒቨርሲቲው ሥራ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተልዕኮውን በብቃትና በቁርጠኝነት መወጣት የሚችል፣ ሙሉ  ስብእና የተላበሰና ኪራይ ሰብሳቢነትን በተግባር የሚዋጋ የህዝብ አገልጋይ ሰራዊት ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ከዚህ አንጻር ስልጠናው አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ለህዳሴው ጉዜ ስኬት የሚያስፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከምንጫቸው ማድረቅ፣ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓቶችን ማጠናከር እንዲሁም በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ወሳኝ መሆኑ በስልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡

የስልጠና ሰነዶቹ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ደሳለኝ ሣሙኤል እና በትምህርት ዘርፍ የሪፎርም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ኤልያስ ግርማ ቀርበዋል፡፡ በስልጠናው ከ100 በላይ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ በየደረጃው ላሉ ሰራተኞችና ተማሪዎች ተከታታይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡና አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡