ስፖርት አካዳሚ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከጋሞ ጎፋ ዞን 17 ወረዳዎች ለተወጣጡ የስፖርት ባለሙያዎች የቅርጫት ኳስ የመጀመሪያ ደረጃ ዳኝነት ስልጠና ከጥር 30-የካቲት 9/2008 ዓ/ም ለአስር ተከታታይ ቀናት  ሰጥቷል፡፡

ለቅርጫት ኳስ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች፣ የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ የዳኞች ምልክቶች፣ የቡድኖች አወቃቀር፣ የአጨዋወት ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በስልጠናው ተዳሰዋል፡፡

በንድፈ ሃሳብ፣ በተግባር እና በአካል ብቃት ተደግፎ የተሰጠው ሥልጠና እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ዳኞች ማፍራት የሚያስችል መሆኑን ሥልጠናውን የሰጡት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ባለሙያ ኢንስትራክተር ሀብተየሱስ ገብሬ ገልፀዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራም ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሴ ታደገ ዳኝነት ትልቅ የሙያ ዘርፍ እንደመሆኑ ትኩረት የሚፈልግና በጨዋታ ሂደት በአግባቡ መተርጎም ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዘርፉን ለማጠናከር በእውቀትና በክህሎት የተሻሉ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ የስፖርት ዓይነቶች የባለሙያዎችን አቅም በትምህርትና ስልጠና ለማጎልበት ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ስፖርት ጽ/ቤት የስፖርት ትምህርትና ስልጠና አስተባባሪ አቶ በረከት በየነ  ዩኒቨርሲቲው ለሙያው ማደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ስልጠናው በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎች በመፍጠር በዞኑ ስፖርትን ለማስፋፋት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወቅቱ በሚፈልገው ደረጃ በየጊዜው በማሳደግ በዘርፉ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ስለ ቅርጫት ኳስ ዳኝነት ሃሳብ ከመቅሰም ባሻገር በተግባር መሥራት መቻላቸውን በመጠቆም የእድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከ17ቱ ወረዳዎች የተወጣጡና በዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ32 በላይ ሰልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን የተዘጋጀላቸውን ሰርተፍኬት ከዕለቱ እንግዶች እጅ ተቀብለዋል፡፡