ከአርባ ምንጭና ከጫሞ  2ኛ ደረጃና መሰናዶ እና ከአባያ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለተወጣጡ 300 ሴት ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠና ከመጋቢት 11- 17/2008 ዓ/ም በሁለት ዙሮች ተሰጥቷል፡፡

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር መምህርት ወ/ሮ ትዝታ እንዳለ ሥልጠናውን በሚሰጡበት ወቅት እንደገለጹት ዓላማው የሴት ተማሪዎችን በራስ የመተማመን ስነ ልቦና ማጎልበት፣ የአቻ ግፊትና የትምህርት ዓለም ችግሮችን መቋቋሚያ ስልት ማስገንዘብ እንዲሁም የሥርዓተ-ፆታ፣ ሥነ-ተዋልዶና የህይወት ክህሎት ጽንሰ ሀሳቦችን በማስረጽ ለተሻለ አፈጻጸም እንዲነሳሱ ማስቻል ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን በተማሪነት ቆይታቸው የገጠማቸውን ተግዳሮቶችና የስኬት መንገዶችን ልምድ የሚያካፍሉበትም ነው፡፡


በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መ/ር አሰግደው ሽመልስ ተማሪዎቹ ስነ-ልቦናዊና ተግባር ተኮር የክህሎት ስልጠና መውሰዳቸው በትምህርታቸውና በማህበራዊ ህይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ተቋቁመው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹ ከስልጠናው በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና ከፍተኛ የስነልቦና መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው በቀጣይነት ባልተዳሰሱ ጉዳች ላይ ታቅዶ በዙር እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡