የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባባር ከክልሉ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ለተወጣጡ 16 ሀኪሞች በሆስፒታሎች የደም አጠቃቀም ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያስችል ስልጠና ከየካቲት 28 - መጋቢት 1/2008 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡

በሆስፒታሎች በየትኛው የህክምና ደረጃ ላይ ለሚገኝ ታካሚ ደም እንደሚታዘዝ፣ በደም ትዕዛዝና አጠቃቀም ወቅት ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ችግሮች ቢከሰቱ መወሰድ ስለሚገባው የመፍትሔ እርምጃዎች በስልጠናው ተካተዋል፡፡ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ሽፈራው እንደገለፁት የደም ባንክ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በቀይ መስቀል ማህበር ሥር በነበረበት ወቅት በዓመት ከ20 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ደም ይሰበሰብ ነበር፡፡

ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ሥር በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በክልል ጤና ቢሮ በሚገኙ የደም ባንኮች አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 126 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ደም ይለግሳሉ፡፡ ምንም እንኳ ደም የማሰባሰብ ሥራ ቢጨምርም በሆስፒታሎች የሀኪሞች እና የደም ባንክ ባለሙያዎች ደምን በአግባቡ የመጠቀም ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ የስልጠናው ዓላማም ክፍተቶቹን በመሙላት በሆስፒታሎች ውጤታማ የአጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖር ማስቻልና የአሰራር ደንብ መዘርጋት ነው፡፡ ስልጠናው ከዚህ ቀደም የተሰጠ ቢሆንም የሰለጠነው የሰው ሃይል ቦታውን ስለሚለቅና በሌሎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች መተካት ስለሚገባው በድጋሚ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡


በህክምናው ዓለም የደም ባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው ያሉት የኮሌጁ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ  ውጤታማ ቀዶ ጥገናና መሰል የዘርፉ አገልግሎቶች እንዲሳኩና የሰውን ልጅ ህይወት ለማዳን በሚደረገው ርብርቦሽ የደም አጠቃቀምና የባለሙያዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው የደም ባንክ አገልገሎት ጥራት ላይ በቂ ግንዛቤ ያስጨበጣቸው መሆኑና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ከሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የመጡት ዶ/ር ሽመልስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው በዓለም አቀፉ የሲዲሲ ፔፕፋር /CDC-PEPFAR/ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የስልጠና ማዕከል በማድረግ የተሰጠ ነው፡፡