የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በአንድ የዶክትሬትና በሁለት የማስተርስ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች የካቲት 12 እና 14 /2008 ዓ/ም ለሁለት ቀናት የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ አካሂዷል፡፡

የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው በዶክትሬት ዲግሪ Animal Nutrition (የእንስሳት ሥነ-ምግብ) ፣ በሁለተኛ ዲግሪ Animal Production (የእንስሳት እርባታ) እና Rural Development & Agricultural Extension (የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን) የትምህርት መስኮች የተከናወነ ሲሆን በሁለተኛ ዲግሪ የትምህር መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል፡፡
የጅማ፣ ሐሮማያና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያዎችና ሌሎች የኮሌጁ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች በተሳተፉበት ግምገማ በትምህርት መስኮቹ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠትና ሥርዓተ ትምህርቱን ለማጽደቅ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች በስፋት ተዳሰዋል፡፡


የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ነጂብ መሐመድ እንደገለጹት የፕሮግራሞቹ መከፈት በዘርፉ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራት የሚያስችል በመሆኑ በተለይ ለሀገሪቱ ግብርና መር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ስለሆነም የፕሮግራሞቹን ጥራት፣ አግባብነትና ተፈጻሚነት ለመወሰን በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻው ቅድመ ዝግጅት የባለሙያዎች አስተያየት፣ ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ ነው፡፡
የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶ አርካቶ እንደገለጹት በተገቢው መንገድ የተቀረጸ ሥርዓተ ትምህርት ለውጤታማ የትምህርት ጥራት መሠረት በመሆኑ በትምህርት ፕሮግራሞቹ ላይ በውስጥና በውጭ ባለሙያዎች ግምገማ መካሄዱ በቀጣይ የቀረቡ ማሻሻያዎችን በማካተት ውጤታማና የዳበረ ሥርዓተ ትምህርት እንዲሆን ያስችላል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት ያለው ከፍተኛ ፍላጎትና በአካባቢው የልማትና የምርምር ሥራዎች ለማከናወን ያለው ቁርጠኝነት በይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው በየዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በክህሎትና በጥራት ሲሰማራ እንደሆነ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ተስፋዬ ለማ ተናግረዋል፡፡ የግብርና ዘርፍን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምርና የሰው ኃይል በማሰልጠን እንዲሁም መንግስት በፖሊሲና በበጀት በመደገፍ ረገድ የተቀናጀ ርብርብ በማድረጋቸው ተስፋ ሰጪ ውጤት የታየ ቢሆንም በይበልጥ ሊሠራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡


በግምገማ መድረኩ እንደተወሳው በየፕሮግራሞቹ የባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ፣ የትምህርት ጥራት ላይ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ እና የፕሮግራም ጥምረትና ተገቢነትን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን በእንስሳት ሥርዓተ ምግብና እርባታ እና በግብርና ኤክስቴንሽንና ገጠር ልማት ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም ጥናትና ምርምሮችን ወደ አካባቢው ህብረተሰብ ዘልቆ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡


ሥርዓተ ትምህርቶቹ ቀደም ሲል የውስጥ ግምገማ የተደረገባቸው ሲሆን በገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዮሐንስ ማሬ፣ በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህራን አቶ ሰይፉ ብርሃኑ እና ዶ/ር ይስሐቅ ከቸሮ አማካኝነት ቀርበዋል፡፡ በግምገማው ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አበጋዝ በየነ፣ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ነጻነት በየሮ እንዲሁም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ተስፋዬ ለማና አቶ ደረጀ ክፍሌ የውጭ ገምጋሚ ሆነው ታድመዋል፡፡ የግምገማው ተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳትና ሙያዊ አስተያየቶችን በመስጠት ውይይት አድርገዋል፡፡