ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር  ለመድኃኒትነት አገልግሎት በሚውሉ ሀገር በቀል ዕጽዋትና በሞሪንጋ /ሽፈራው/ ተክል ዙሪያ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚዬም አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡ Click here to see the News Video.

የሲምፖዚዬሙ ዋና አላማ ተመራማሪዎችን በማቀራረብ ለሕክምና አገልግሎት በሚውሉ ሀገር በቀል ዕጽዋትና በሞሪንጋ/ሽፈራው/ተክል ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት፣ በዘርፉ የሀገሪቱን የምርምር አቅም ለማሳደግ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የጥናትና ምርምር ቡድን  ለመመስረትና የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የታገዙ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ለማጎልበት በትኩረት እየሠሩ ነው፡፡ የሀገሪቱን የህክምና ዘርፍ ለመደገፍ በጨንቻ ወረዳ በግርጫ አካባቢ በደጋ ፍራፍሬ፣  በጓሮ አትክልትና ለመድሃኒትነት በሚያገለግሉ ዕጽዋት ዙሪያ የሚሰራ የምርምር ማዕከል ተቋቁሟል፡፡ የማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረግ ሀገሪቱ ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት በማምረት ኢንዱስትሪውን እንድትቀላቀል ያስችላታል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪና የሲምፖዚየሙ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀፍቶም  ገ/ኪሮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመድሃኒትነት ይዘት ያላቸው ዕጽዋትና ሞሪንጋን/ሽፈራው/ እንደ አንድ የምርምር አቅጣጫ በመውሰድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ግንባታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኘው የተለያዩ የምርምር ማዕከላት ዘርፉን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እንዲደግፉና እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሲምፖዚዬሙ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ የምርምር ተቋማት የመጡ ተመራማሪዎች በስራው ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ፣ የተሻለ ልምድ እንዲያካብቱና አብረው ለመስራት እንዲችሉ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዘርፉ የተሰሩ ስራዎችን በመለየት ጉድለትና ማሻሻያዎችን ማስቀመጥ፣ ውጤታማ የምርምር ውጤቶችን በአገር አቀፍና አለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ ማሳተም ብሎም ወደ ህብረተሰቡ የማውረድ ስራ ይጠበቃል፡፡

በሲምፖዚዬሙ በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር አጌና አንጁሎን ጨምሮ ከተለያዩዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ 16  ጥናት አቅራቢዎች ጥናትና ምርምሮችን አቅርበዋል፡፡ ስድስት ሺህ ሀገር በቀል ዕጽዋት ያሏት ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት የሚሆኑት በመድሃኒትነት እንደተመዘገቡ በሲምፖዚዬሙ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም በደን ምርምር፣  በአካባቢ ብክለት ጥበቃ አስተዳዳር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች በርካታ የምርምር ዘርፎች ላይ የሚሰራ ሲሆን መድኃኒትነት ያላቸው ዕጽዋት ጥናት በተቋሙ የደን ልማት አጠቃቀም ዳይሬክተር ስር እንጨት ያልሆኑ የደን ውጤቶች ጋር አብሮ የሚጠና የምርምር ዘርፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡  በአካባቢና የደን ምርምር ዙሪያ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት መፈረሙን እና በተቋማቸው የምርምር ንድፈ ሀሣቦች ላይ መሥራት ለሚፈልጉ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተቋሙ ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ውብዓለም ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው የስራ ክፍል ሃላፊዎችና ምሁራን በሲምፖዚዬሙ ተገኝተዋል፡፡