የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች በሰው ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች አፈፃፀም በ17/07/2008 ዓ/ም የአንድ ቀን ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ሥልጠናው በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና የተሰጡ መፍትሔዎችን በማቀናጀት የተዘጋጀ በመሆኑ በአፈፃፀም ዙሪያ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል ብለዋል፡፡

በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የአደረጃጀት፣ ሥራ ምዘናና ክፍያ ጥናት ቢሮ ኃላፊ አቶ መብራቱ ካሳ ባቀረቡት የሥልጠና ሰነድ እንደተገለጸው የሰው ሀብት ሥራ አመራር የአንድን ተቋም የሰው ሀብት ዕቅድ፣ ምልመላና መረጣ፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም፣ የሠራተኛ ደህንነት፣ ጤንነት እንዲሁም የሠራተኛ ግንኙነት ተግባራት ያከናውናል፡፡

በበርካታ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሰው ሀብት ሥራ አመራር በግንዛቤ እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች መመሪያና ደንብ ያልተከተሉ የአፈፃፀም ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዳዲስ የሥራ መደብ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል በተደጋጋሚና በተበጣጠሰ ሁኔታ በቢፒአር ጥናት ያልተደገፉ የሥራ መደብ ጥያቄዎችን ማቅረብ፣ ለሚያቀርቧቸው ልዩ ልዩ የሥራ ምደባ ጥያቄዎች አስፈላጊ መረጃዎችን አሟልቶ አለመቅረብ እና ስምንት ሰዓት የማያሠሩ የሥራ መደቦች እንዲፈቀዱ መጠየቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አግባብነት በሌለው የትምህርት ዝግጅት እና ሥራ ልምድ የቅጥር/ዕድገት ውሳኔ መስጠት፣ ዝቅተኛው ተፈላጊ ችሎታ የሌላቸውን ሠራተኞች መመደብ፣ በታሳቢ ቅጥር መፈፀም፣ ሠራተኞች የሙከራ ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ማዘዋወር፣ ለ6 ወር ሙከራ የተቀጠሩ ሠራተኞች በወቅቱ ግምገማ በማድረግ ውጤት አለመሙላት እንዲሁም በውስጥ ዝውውር ሠራተኞችን ከሙያው ጋር ተዛማጅ ባልሆነ ቦታ ላይ መመደብ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የሚፈፀሙ ስህተቶች እንደሆኑ በሰነዱ ተመልክቷል፡፡

በሥልጠናው የሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99ን ለማሻሻል የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል፡፡ ለአፈፃፀም የማያመቹ፣ ግልጽነት የሚጎድላቸውና የማያሠሩ አንቀፆች ማሻሻያ እንደተደረገባቸውና በተለይ ሴት የመንግሥት ሠራተኞችን በእጅጉ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንቀፆች በረቂቅ አዋጁ መካተታቸው ተገልጿል፡፡