በ2008 ዓ/ም የስድስት ወራት የፋይናንስና በጀት፣ የግዥ እና የንብረት አስተዳደር አፈፃፀም ኦዲት ላይ ሚያዚያ 3/2008 ዓ/ም የግማሽ ቀን ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የጉባኤው ዓላማ የፋይናንስና በጀት፣ የግዥ እና ንብረት አስተዳደር አፈፃፀም በመመሪያና ደንብ መሠረት መከናወኑን መገምገም፣ የታዩ ግድፈቶችን ማረምና የተሻሉ አፈፃፀሞችን በማጠናከር ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምና የንብረት አስተዳደር ሥርዓትን ማጎልበት መሆኑን የኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ተረፈች መንግስቱ ገልፀዋል፡፡

በጉባዔው የ2008 ዓ/ም የመጀመሪያ ስድስት ወራት የአላቂ ንብረት እና የፋይናንስና በጀት አፈፃፀምን በተመለከተ የውስጥ ኦዲት ሪፖርት በባለሙያዎች ቀርቧል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት ግኝቶች፣ ስጋቶችና የማሻሻያ ሃሳቦች ቀርበው ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች እና የፋይናንስ፣ የግዥና ንብረት ዘርፍ አስተባባሪዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥንቃቄ የጎደለው የአላቂ ንብረት አጠቃቀም፣ አግባብነት የሌለው የውሎ አበልና የትርፍ ሰዓት አከፋፈል፣ ከተቋሙ ዕቅድ ውጭ የተፈፀሙ ግዥዎች፣ በተለያየ መጠን የተሰበሰቡ የዋጋ ማቅረቢያዎች እንዲሁም ባልታደሰ የንግድ ፈቃድ የተመዘገቡ፣ ኦንላይን ምዝገባ ያላካሄዱና ከንግድ ዘርፋቸው ውጪ ተወዳድረው ያሸነፉ ድርጅቶች ከታዩ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ጥንቃቄ የተሞላበት የንብረት አያያዝና አጠቃቀም እንዲዳብር ግንዛቤ ማስፋትና ክትትል ማድረግ፣ የግዥ ሥርዓቱ በእቅድና በበጀት ኮድ መሰረት የሚመራበትን ሂደት ማጠናከር እና የሰነድ ተገቢነትን ማረጋገጥ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ይህን መሰል የኦዲት መውጫ ጉባኤ መካሄዱ ለመማማር ምቹ መድረክ የሚፈጥር፣ የውስጥ አሰራሩን ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመምራት የሚያስችልና የለውጥ ሂደቱ አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጉባኤው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የየኮሌጁና የኢንስቲትዩቱ የፋይናንስ፣ የግዥና ንብረት ዘርፍ አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል፡፡