እንሰት ፓርክ ፕሮጀክት የመጀመሪያውን የሁለት ቀናት ብሔራዊ አውደ ጥናት ከመጋቢት 27-28/2008 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ የዓውደ ጥናቱ ዓላማ የእንሰት ዋግ በሽታን በመከላከልና የአመራረት ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ በማፈላለግ የእንሰት ምርታማነትን ለማሳደግ የጋራ ግንዛቤና አቋም መፍጠር ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርሶ አደሮች ከመንግስታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት በተፈጥሮ አጠባበቅ ዙሪያ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚገባ ጠቅሰው የእንሰት ፓርክ ፕሮጀክትም ከድጋፎቹ አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል እንደገለፁት የብዝሃ-ሕይወት ጥበቃን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ለማህበራዊ ደህንነት ወሳኝ በመሆኑ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጀንዳ ሊሆን ችሏል፡፡ የእንሰት ጥበቃ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሳይንቲስት ዶ/ር እንዳለ ገብሬ በእንሰት አጠውላጊው የባክቴሪያ ዋግ/ባክቴሪያ ዊልት/ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ሀገር በቀል የንፅሕና አያያዝ ዘዴዎችና የተቀናጁ የተባይ አስተዳደር ዘዴዎች ብቻ ዋግን የማያጠፉ ሲሆን  በኡጋንዳ በሙዝ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ በሆነው በጂን የማዳቀል ዘዴ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡ የእንሰት ተክል ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሀገራት ለምግብነት በሠፊው የሚዘወተር ባለመሆኑና በተክሉ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቂ ሳይንሳዊ ምርምር አለመከናወኑ ለበሽታው እስከአሁን  ዘላቂ መፍትሔ እንዳይገኝ አድርጓል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ሰብስበው ደምሰው እንዳሉት በቀጣይ ጊዜያት በእንሰት ምርት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን በተክሉ ላይ የሚሠሩ ምርምሮች ሠፊ አቀራረብ ያላቸው እንዲሁም ስነ-ምህዳራዊ፣ መልክዓ-ምድራዊና ሰው ሰራሽ ጉዳዮችን በግልፅ የሚያብራሩ መሆን አለባቸው፡፡ እንሰት አምራች ያልሆኑ አካባቢዎች በድርቅ የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑም የእንሰት ተክልን ማስፋፋት አስፈላጊ ነው፡፡

የብዝሃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል እንዲሁም የእንሰት ፓርክ መስራችና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ፕሮጀክቱ የእንሰት ምርት ሂደትን የተሻለና ዘመናዊ በማድረግ ምርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበያ የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ብሎም ግንዛቤን ለማስፋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በጨንቻ ወረዳና በአካባቢው በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌያት አርሶአደሮችን በ12 የእንሰት ማህበራት አደራጅቶ ህጋዊ እውቅና የሰጠ ሲሆን የእንሰት ዘረመል ባንክ (ጂን ባንክ)  አቋቁሟል፡፡

በዓውደ ጥናቱ በተዛማጅ የምርምር ርዕሶች በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የአዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ ወላይታና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአረካ እና አርባ ምንጭ የምርምር ኢንስቲትዩት ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በማጠናቀቂያውም ጨንቻ የሚገኘው የእንሰት ፓርክ የተጎበኘ ሲሆን ከአካባቢው አርሶአደሮች  ጋር የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል፡፡