የ2006 ዓ/ም ባች የምህንድስና ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የነበራቸውን የ2 ዓመት ተኩል ውጤታማ ቆይታ በማስመልከት በዋናው ግቢ መጋቢት 17/2008 ዓ/ም ዕለቱን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የፕሮግራሙ ዓላማ ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ብቁና ተወዳዳሪ ከመሆናቸው ባሻገር በሥነ-ምግባር ታንፀው ዩኒቨርሲቲውን ብሎም ሀገራቸውን በበጎ ጎን እንዲያስጠሩ ማገዝ መሆኑን የተማሪዎች ህብረት አካዳሚክ ተጠሪና የፕሮግራሙ ዋና አስተባባሪ ተማሪ ማህደር ዘነበ ተናግሯል፡፡ ቀጣይ ባቾች ተሞክሮ ወስደው በመፈቃቀር፣ በመቻቻልና በዓላማ ፅናት በዩኒቨርሲቲው ስኬታማ የመማር ማስተማር ሥርዓት ለማጎልበት ጥረት እንዲያደርጉም ያነሳሳል፡፡

ተማሪዎቹ በቆይታቸው አምስት ሴሚስቴሮችን አጠናቀው ከመርሃግብሩ አጋማሽ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ቀጣዩን የትምህርት ዘመን ጠንክረው በመስራት ለውጤት እንዲበቁና በስነ-ምግባርም ሆነ በጎ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ተምሳሌት እንዲሆኑ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ዮርዳኖስ መኩሪያው አሳስበዋል፡፡

የሁለቱም ፆታዎች እግር ኳስ ውድድር፣ የታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሥፍራዎች ትምህርታዊ ጉብኝት፣ ችግኝ ተከላ እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች የፕሮግራሙ አካል ነበሩ፡፡ በዕለቱ በዋናው ግቢ 250 ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በከተማው ለሚገኙ አቅመ ደካማና ችግረኞች የሚከፋፈሉ አልባሳት ተሰባስበው ለበጎ አድራጎት ክበብ ተበርክተዋል፡፡ በትምህርታዊ ጉዞው የኮንሶና ጨንቻ ወረዳዎች፣ አዞ እርባታ እና 40ዎቹ ምንጮች ጉብኝት ተደርጓል፡፡ ጉዞው የየትምህርት ክፍሎቹን መምህራን አሳትፎ የተከናወነ በመሆኑ በተማሪዎችና በመምህራን መካከል መቀራረብን በመፍጠር ለሥኬታማ መማር ማስተማር እገዛ እንደሚያደርግ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት በቀደሙት ባቾች ባልተለመደ መልኩ በዓሉ ልማታዊና የበጎ አድራጎት ተግባራት በማከናወን መከበሩ የዘንድሮውን ባች ለየት ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ቀጣይ ባቾችም ይህንን ፈለግ ተከትለው በተሻለና አስተማሪ በሆነ መንገድ ለማክበር ዝግጅት እንዲያደርጉም መክረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማገባደጃ በበጎ አድራጎት ተግባር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የ3ኛ ዓመት ምህንድስና ተማሪዎች፣ ለአካባቢ ልማትና ጥበቃ ክበብ፣ ለቻሪቲ ክበብ፣ ለሰላም ፎረም እና ለስፖርት አካዳሚ የተማሪዎች ህብረት የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡