የዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነት ጽ/ቤት ከጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ለ150 የፀጥታና ደህንነት አባላት በወንጀል ምንነትና መከላከል፣ በመሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ሰልፍ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከመጋቢት 8/2008 ዓ/ም ጀምሮ ለ7 ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የስልጠናው ዓላማ የፀጥታና ደህንነት አባላት በመሳሪያ አያያዝ፣ በወታደራዊ አሰላለፍ፣ በአልሞ መተኮስ፣ በወታደራዊ ስነ-ምግባር እንዲሁም በተገልጋይ አያያዝ ስልጠና አግኝተው ተመጣጣኝ አቅም እንዲኖራቸውና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በብቃት ለመከላከል እንዲቻል ማድረግ መሆኑን የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሻለቃ አበበ አማረ ገልፀዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በመክፈቻ ንግግራቸው የዩኒቨርሲቲውን ፀጥታና ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ለማስፈፀም ስልጠናዎችን በመስጠት የማብቃት ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው በቀጥታ ከስራው ጋር የተገናኘ በመሆኑ በሰልጣኞቹ ላይ ጉልህ ለውጥ የሚያመጣና ብቁ አባላትን ለማፍራት የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ በዘላቂነት እንዲቀጥል ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ስራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር ፊልቨር ቁጮ ወንጀል በአንድ ሃገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከባድ በመሆኑ ወንጀልን የመከላከል ተግባር የሁሉም ዜጋ ግዴታና ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡ በተቋማት አካባቢ የሚከሰቱ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ የተቋሙ አስተዳደር፣ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው የፀጥታ ሃይሎች አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም በዋናነት ግን የጥበቃ ሰራተኞች ኃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በተቋማት አካባቢ አዘውትረው የሚከሰቱ የወንጀል አይነቶች፣ መንስኤና መፍትሄያቸው እና የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ትርጉምና አስፈላጊነትን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የነበራቸውን የክህሎት ክፍተት በመቅረፍ ስራቸውን በንቃት ለመስራት የሚያበቃቸው መሆኑን ገልጸው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወንጀልን በመከላከል ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ ወታደራዊ ሰልፍ፣ የመሳሪያ መፍታትና መግጠም እንዲሁም ኢላማን አስመልክቶ ሰፊ የተግባር ልምምድ አድርገዋል፡፡