የተቀናጀ የትምህርትና ቴክኖሎጂ አመራርን ለማጠናከር ከሁሉም ካምፓስ የተወጣጡ የ1ለ5ና የልማት ቡድን ተጠሪ ተማሪዎች እንዲሁም የአደረጃጀቱ አስተባባሪ መምህራን መጋቢት 04/2008 ዓ/ም ከተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬትና ከፕሬዝደንት ጽ/ቤት ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የውይይቱ ዓላማ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት በአንደኛው ወሰነ ትምህርት ያከናወናቸውን ምርጥ ተሞክሮዎች   ለማዳበርና ከታዩ ድክመቶች በመማር ለለውጥ መሥራት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡

በ1ኛው ወሰነ ትምህርት ሁሉም የትምህርት ክፍሎች የ 1ለ5 እና የለውጥ ቡድን አደረጃጀቶችን በተግባር መጠቀማቸው እና የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መጠነ መባረር በ2007 ዓ/ም ከነበረበት 3.25 በ2008 ዓ/ም ወደ 2.48 ሊቀንስ መቻሉ ጠንካራ አፈፃፀም ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሌላ በኩል ሳምንታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርቶችን በወቅቱ ያለማቅረብና በሁሉም አደረጃጀቶች ላይ የቁጥጥርና ክትትል መላላት ክፍተቶች በመኖራቸው በቀጣይ ትኩረት የሚሹ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ምርጥ ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ የእቅድ አፈፃፀሙ በየጊዜው እንዲሻሻል የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ቡድኑን የማብቃት ሥራ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ መሆኑን የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደባልቄ ዳልጮ  ገልፀዋል፡፡

የግብኣት አለመሟላት፣ በአንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ቤተ-ሙከራዎች በአግባቡ አለመደራጀት፣ ለተማሪዎች የሚሰጡ አሳይመንቶች መደራረብና መሰል ችግሮች በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስተው ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በውይይቱ የሁሉም ኮሌጆች ዲኖች፣ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አስተባባሪ ተማሪዎች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በድምሩ 320 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡