የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ እንዲሁም ከዞኑ 15 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤቶች ለተወጣጡ 47 የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና  የጽ/ቤት ኃላፊዎች  ከታህሳስ 4-6/2009 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሥልጠናው ዓላማ መሠረታዊ የጋዜጠኝነትና የህዝብ ግንኙነት አተገባበር ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣ የዜና አፃፃፍና አዘገጃጀት ክህሎት ማዳበርና የሙያዊ ሥነ-ምግባር መርሆዎችንና ደንቦችን በመተግበር ተዓማኒና ሚዛናዊ መረጃ እንዲቀርብ ማስቻል መሆኑን የኮሌጁ ማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መምህር አሰግደው ሽመልስ ገልፀዋል፡፡

አስተባባሪው በልማታዊ ጋዜጠኝነትና ፍልስፍና፣ የልማታዊ ተግባቦት ምንነትና ትግበራ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ የህዝብ አስተያየት አሰባሰብ ዘዴና ለሚዲያ ማቅረቢያ መንገድ፣ የማኅበረሰብ ሬድዮ ጥቅም እና የሚዲያ ልማት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ/ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጣሰው ጨቾ በበኩላቸው ሥልጠናው የዞኑን ማኀበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በሚዲያ ይበልጥ ለማስተዋወቅና የገፅታ ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኮሌጁ የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ መምህር አቶ መኮንን ተካ የህዝብ ግንኙነት ምንነትና ተግባራት፣ የባለሙያዎች የሥነ-ምግባር መርሆዎችና ደንቦች፣ በቀውስ ወቅት የሚዲያ አያያዝ (Crisis Communication) ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን መምህር ሰመረ አምሃ በበኩላቸው የዜና ባህሪያትና የአፃፃፍ ስልቶች፣ የዜና ጥቅም፣ የዜና መስፈርቶች፣ የዜና ምንጮችና አውታሮች የሚሉ ርዕሶችን አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ታዳሚዎች በቀላሉ ሊረዱ በሚችሉት አገላለፅ ማቅረብና የተቋሙን ገፅታ መገንባት ተቀዳሚ ተግባር አድርገው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሠልጣኞቹ አሳስበዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በተግባር ሊለወጥ የሚችል ጠቃሚ ሙያዊ ግንዛቤ እንደጨበጡ ተናግረዋል፡፡ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡