የስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ከተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በዕቅድ ዝግጅት፣ በBSC ውጤት ተኮር ሥርዓት የሥራ አፈጻጸም ምዘና እንዲሁም በቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ ዙሪያ ከታህሳስ 6-7/2009 ዓ.ም ለኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ቡድን መሪዎችና አስተባባሪዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሥልጠናው ዓላማ ወጥነት ያለው የቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ በሁሉም ኮሌጆች፣ ዳይሬክቶሬቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና በስፖርት አካዳሚ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ በማስቀጠል የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እና ሳይንሳዊ የእቅድ አዘገጃጀትና ውጤት ተኮር አፈጻጸም ምዘና በማጠናከር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መፍጠር መሆኑን የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሞ ቀልቦ ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኞች የዕቅድ ዝግጅት እና የውጤት ተኮር ሥርዓት ምንነትና ዓላማዎች፣ የአፈጻጸም ምዘና መርሆዎችና ስምምነቶች፣ የቡድን መሪዎችና የ1ለ5 ቡድን መሪዎች ተግባርና ኃላፊነቶች፣ የBSC ውጤት ተኮር አፈጻጸም ምዘና ፎርማቶች ላይ ዕውቀትና ክህሎት ያገኙ ሲሆን በቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ የታዩ ክፍተቶችና ጠንካራ አፈጻጸሞች ላይም ተወያይተዋል፡፡

ዕቅድ ለአንድ ሰራተኛ ዋነኛ የቅርብ አለቃ ሲሆን ዓመታዊ፣ ወርሃዊ፣ ሳምንታዊና ዕለታዊ ሥራዎችን የሚመራና የሚቆጣጠር መሳሪያ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም የሥራ ክፍሎች ልማዳዊ የዕቅድ አዘገጃጀትና የውጤት ተኮር አፈጻጸም ምዘናን በማስቀረት ሳይንሳዊ የእቅድ ዝግጅትና የውጤት ተኮር አፈጻጸም ምዘና በመዘርጋት እንዲሁም ሠራተኞች ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር በመቀየር የእቅድ ትግበራን መረጃ መሰረት ያደረገ የአፈጻጸም ምዘና መሠራት አለበት፡፡ ፕሬዝደንቱ የቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሰራዊት አደረጃጀትን አጠናክሮ በመቀጠል፣ ክፍተቶችን በመሙላትና የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከልማዳዊ የዕቅድ ዝግጅትና የአፈፃፀም ምዘና ወደ ሳይንሳዊ የውጤት ተኮር አሰራር በመሸጋገር የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትክክለኛ የውጤት ምዘና ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም የተቀላጠፈ የቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አቅም ፈጥሮልናልም ብለዋል፡፡

በስልጠናው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የካምፓስ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ አስተባባሪዎችና የአንድ ለአምስት ቡድን መሪዎች ተገኝተዋል፡፡