በ2008 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ 56 የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ታህሳስ 13/2009 ዓ/ም የእውቅና ምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ መምህራን፣ የአስተዳር ሠራተኞችና አመራሮች እውቅና መስጠት ለቀጣይ ሥራ አፈፃፀም መሻሻልና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በእውቅና አሰጣጥና የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡ ሽልማቱ የጎላ አፈፃፀም ያሳዩ ጥቂት ፈፃሚዎችን ያካተተ ቢሆንም ሌሎች በርካታ ትጉህና በየዘርፋቸው ጠንካራ አፈፃፀም ያላቸው ሠራተኞችም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በየዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት ያላቸው እንዲሁም ትምህርታቸውን ጨርሰው ሲመረቁ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን መሸለም የተለመደ ቢሆንም ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የሽልማት ፕሮግራም ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በቀጣይም የለውጥ ሥራዎችና አበይት ተግባራትን በማከናወን ጠንካራ አፈፃፀም ለሚያስመዘግቡ የሥራ ክፍሎችና ግለሰቦች እውቅና የመስጠት ሥርዓት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተሸላሚዎቹ በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ የሥራ ተነሳሽነትን በመጨመር በሠራተኞች መካከል ጤናማ የፉክክር መንፈስን ይፈጥራል፤ ሁሉም ሠራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በባለቤትነት እንዲወጡ የሚያነቃቃ ነውም ብለዋል፡፡