የተማሪዎች ኅብረት የ2009 የትምህርት ዘመን የአስፈፃሚ አባላት ስብሰባ የመጀመሪያ ዙር ታህሳስ 9/2009 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ የስብሰባው ዓላማ የተማሪዎች ኅብረት የሥራና የበጀት ዕቅዶችን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች በማስገምገም ማጸደቅ እና ክፍተቶች ባሉበት የሥራ አስፈጻሚ አመራር ቦታዎች ላይ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን የኅብረቱ ፕሬዝደንት ተማሪ ጌታቸው ወርቁ ገልጿል፡፡ ኅብረቱ በዓመት አራት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ የሚያካሂድ ሲሆን የ2009 በጀት ዓመት 1ኛ ዙር ስብሰባ በዓመቱ መጀመሪያ መከናወን ሲገባው በሥራዎች መደረረብ ምክንያት መዘግየቱን ፕሬዝደንቱ ተናግሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዕለቱ ዓመታዊ የሥራና በጀት ዕቅዶች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የምክትል አፈ-ጉባኤና የኦዲተር ምርጫ እንዲሁም በማሟያ ምርጫ የተመረጡ የሁሉም ካምፓሶች አባላት ትውውቅ ተከናውኗል፡፡ ከጫሞ ካምፓስ ተማሪ የማነ ብርሃኑ ምክትል አፈ-ጉባኤ እና ተማሪ ደረጀ ከምባታ ኦዲተር ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በዓመታዊ ዕቅዱ በተማሪዎች አገልግሎት፣ በአካዳሚክ፣ በዲሲፕሊን፣ በስፖርትና መዝናኛ፣ በሥርዓተ-ጾታ፣ በአካል ጉዳተኞች እና ልዩ ድጋፍ፣ በፋይናንስና ገቢ አሰባሰብ፣ በጤና፣ በዶርሚተሪ እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የታቀዱ ዝርዝር ተግባራት እና ስድስት መቶ ሰባ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ ብር (678, 650) ዓመታዊ በጀት ፀድቋል

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲያችን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ፣ የትምህርት ግብዓቶች የተሟሉ እንዲሆኑ፣ ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲሰፍን ወዘተ የዩኒቨርሲቲያችን አመራርና ሠራተኛ በቁርጠኝነት እየተጋ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቻችንም የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ተልዕኮውን በማገዝ ረገድ የተማሪዎች ኅብረት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በመሆኑም በ2009 የትምህርት ዘመን አንድም ብክነትና ክፍተቶች ሳይኖሩ ዕቅዶችን ወደ ተግባር በመቀየር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የኅብረቱ አባላት በሰጡት አስተያየት ዓመታዊ ዕቅዱ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የመማር ማስተማር ሂደቱን በመልካም ሁኔታ እንዲጓዝ የሚያግዝ ነው፡፡ በመሆኑም ዕቅዶቹን ለማስፈፀምና የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ኅብረቱ ካለፉት ጊዜያት በበለጠ ተግቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የተማሪዎች ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡