ዩኒቨርሲቲው 11ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክብረ በዓል ‹‹ህገ-መንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል ህዳር 26/2009 ዓ.ም በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በድምቀት አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የፓናል ውይይት፣ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ ስፖርታዊ የገመድ ጉተታ ውድድር፣ የቴኳንዶ ማርሻል አርት ትዕይት እንዲሁም በብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳት የደመቁ ባህላዊ ጭፈራዎችና ትዕይንቶች የበዓሉ አካል ነበሩ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ውብ የሆነውን ልዩ ልዩ የሀገራችን ህዝቦች ባህል በማሳየት እርስ በርስ ተሳስቦ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖርና የመማር ባህላችንን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ለህዝባችን መልካም ምሳሌ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና የህዳሴያችን መሰረት የሆነውን ህገ-መንግሥታችንን አክብረንና አስከብረን በተሠማራንበት መስክ ሁሉ ግንባር ቀደም መሆን ይገባናልም ብለዋል፡፡

ኅዳር 29 የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን የማሳደግ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እና በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ የመሆን ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት ቀን መሆኑን የጋሞ ጎፋ ዞን ደኢህዴን ንዑስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ሀኪሜ አየለ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ጠባብነት፣ ትምክተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሐይማኖት አክራሪነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመታገል የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የህገ-መንግስት ምንነት፣ ዓላማ፣ ቱሩፋቶችና እና የሀገራችን ህገ-መንግስት ከየት ወዴት በሚሉ ርዕሶች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ህገ-መንግሥቱን በዳሰሰው የጥያቄና መልስ ውድድር ከአንደኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ለያዙ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የታዳሚዎችን ቀልብ የሳበው በዩኒቨርሲቲው በሠላም ፎረም አባላት እና በፀጥታና ደህንነት ሠራተኞች መካከል የተካሄደው ስፖርታዊ የገመድ ጉተታ ውድድር በሠላም ፎረም አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ኤፍ ቴኳንዶ ማርሻል አርት ቡድን አዝናኝ ትዕይንቶችን አሳይተዋል፡፡ ተማሪዎች የብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት እና ባህላዊ ውዝዋዜ በማሳየት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተዋል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ህገ-መንግስቱ ባጎናፀፋቸው መብት ተቀብረውና ተረስተው የነበሩ ቋንቋዎችና ባህሎች እንዲሁም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ኋላ ቀር አካባቢዎች ዕኩል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የህገ መንግሥቱን ቱርፋቶች በመጠበቅና በማስቀጠል የኢትዮጵያን ህዳሴ ዕውን ለማድረግ ተግተን መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

በክብረ በዓሉ የጋሞ ጎፋ ዞን የደኢህዴን ንዑስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተወካይ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የሁሉም ካምፓሶች  መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡