የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አካባቢ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሻይ ቡና እንዲሁም በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ከተሰማሩ ነጋዴዎች ጋር ኤች አይ ቪ/ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ግንዛቤ ለመፍጠርና የዘመቻው አካል እንዲሆኑ ለማድረግ የጋራ ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የውይይቱ ዓላማ የንግዱ ማህበረሰብ በኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከል ላይ በንቃት በመሳተፍ ራሳቸውንና የሚያገለግሏቸውን ተማሪዎች ከበሽታው እንዲጠብቁ የሚያስችል አቅም መፍጠርና ከቀድሞው በተሻለ ጥንቃቄ እንዲኖራቸው ማስቻል መሆኑን የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

ተወያዮቹ በዓለም ዓቀፍ፣ ሀገር አቀፍ፣ በክልልና በዞን እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ ደረጃ የኤች አይ ቪ ሥርጭት በነጋዴው ህብረተሰብ ዘንድ ምን እንደሚመስል መሰረታዊ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በነጋዴው ማህበረሰብና በሚያገለግሏቸው ተማሪዎች አካባቢ የሚታዩ ለኤች አይ ቪ/ኤድስ እና የሥነ-ተዋልዶ ችግሮች አጋላጭ ባህሪያት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋል ሥርዓት አልባ አለባበስ፣ በሰዋራ ሥፍራዎች ጥንድ ሆኖ ማምሸት፣ የጫት መቃሚያና ሺሻ ቤቶች መበራከት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ቤት ተከራይቶ መኖር ከአጋላጭ ባህሪያት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

አንዳንድ ተማሪዎች በትምህርት ሰዓት በሻይ ቡና ሰበብ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ብዙ ሰዓት ማባከናቸው እንዲሁም በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው አልባሌ ቦታዎች ማምሸትና ማደራቸው ሥርጭቱ  ይበልጥ እንዲስፋፋ የሚያደርግ መሆኑን ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተለይም የመኝታ ክፍል፣ የምግብ ቤትና የጥበቃ ሠራኞች እንዲሁም የአካባቢው ነጋዴዎች በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የቫይረሱን ሥርጭት በመከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ እንደ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡