አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ ፕሮግራምን የሚሰጡ 17 ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ ከግንቦት 18-19/2009 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ዓውደ ጥናት አሰናድቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም በዩኒቨርሲቲዎቹ የተለያዩ መጠሪያዎችን ይዞ በአምስት እና በአምስት ዓመት ተኩል ጊዜያት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ይህም በዩኒቨርሲቲዎችና በተማሪዎቹ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ ፕሮግራሞች መጣጣም የሚገባቸው መሆኑን በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ፕሮግራሙ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መልኩ በአምስት ዓመታት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲዎች የየራሳቸውን ክለሳ በማድረግ መነሻ ሰነዶችን አዘጋጅተዋል፡፡ በተበታተነ መልኩ የተከናወኑ ክለሳዎችን በጥቅል ፈር ለማስያዝ ዓውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ግዛው ፍቅሬ ተናግረዋል፡፡

የሥርዓተ ትምህርት ክለሳው ትምህርቱ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ በሆነ መልኩ እንዲሰጥ የሚያደርግ ሲሆን ይህም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች በሥራ ዓለምም ሆነ በቀጣይ የትምህርት ሂደት ልዩነት ሳይፈጠር በተቀራራቢ ፕሮግራም ብቁ ሆነው እንዲወጡ ያስችላል፡፡ በተዘበራረቀ ሥርዓተ ትምህርት ምክንያት አዳጋች የነበረውን የተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ወደ ዩኒቨርሲቲ የዝውውር ጥያቄዎችን በቀላሉ ለማስተናገድም ይረዳል፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ መጠሪያዎችን በማስቀረት በተማሪዎች የምስክር ወረቀት ላይ የሚያርፈው ስም አንድ እንዲሆንም ይደረጋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየሠራበት ያለው ሥርዓተ ትምህርት በ11 ሴሚስተር የሚጠናቀቅና የተማሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓትም በዓመቱ አጋማሽ የሚከናወን በመሆኑ በተማሪዎች ላይ ተጨማሪ ጫና እንደሚፈጥር የተናገሩት አቶ ግዛው ማሻሻያው ሲደረግ ይህንን ጫና እንዲሁም ተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን ወጪዎች ይቀንሳል ብለዋል፡፡

የፕሮግራሙ አጠቃላይ የአምስት ዓመታት ኮርሶች እና የሚጨመሩ፣ የሚቀነሱ እንዲሁም የሚዋሃዱ ኮርሶች ላይ የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በቡድን በመከፋፈል የዩኒቨርሲቲዎቻቸውን ልምድና በሥነ-ህንፃ ዘርፍ የወቅቱን የገበያ ፍላጎት መሠረት አድርገው ተወያይተዋል፡፡ በአስተያየቶቹ መሠረት ዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ትምህርቱን ረቂቅ አዘጋጅቶ ለተሳታፊ ዩኒቨርሲቲዎችና ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚልክ ሲሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ሲጠናቀቁ የ2010 አዲስ ገቢ ተማሪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡