በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የባህል መድሃኒት ጥናት፣ ጥበቃና ማበልፀግን የተመለከተ ዓውደ ጥናት ከነሐሴ 19-20/2009 ዓ/ም ለሁለተኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡

የጉባዔው ዋና ዓላማ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ሀብቱን በማጥናትና በመሰነድ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቻልበትን ስልት በማስቀመጥ እና ሙሉ ግብዓቱን ወደ ፖሊሲ ደረጃ በማሳደግ የባህል መድሃኒቶችና የባህል ህክምና ላይ ትኩረቱን ያደረገ አንድ ሀገራዊ አደረጃጀት መፍጠር እንደሆነ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የባህላዊ መድሃኒቶች እና የባህላዊ ህክምና እንዲሁም መሰል ሀገር በቀል እውቀት የብሄራዊ ሀብት አካል በመሆን ለልማቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ባህላዊ መድሃኒት እና ህክምና ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የዘርፉ ምሁራን እያደረጉ ያሉት ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚ/ር ዴኤታው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ከጉባኤው የሚገኘው ግንዛቤ ሀገራችን በሣይንስና ቴክኖሎጂ ለመበልፀግ ለምታደርገው ጥረት የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የባህላዊ መድሃኒት እውቀት ዘመናትን አልፎ በቅብብሎሽ መልክ ሲተላለፍ የኖረ ብሔራዊ ሀብት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ80 በመቶ በላይ የሆነው ህዝብ በባህላዊ መድሃኒቶች እና በባህላዊ ህክምና የሚጠቀም መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ጥቅም ላይ የሚውሉትን የባህል መድሃኒቶችና በመሰል ዘርፎች ያለውን ሀገር በቀል እውቀት በማልማት ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ ነው፡፡ የባህል መድሃኒቶች እና የባህል ህክምና በሥርዓተ ትምህርት ካለመካተታቸውም በተጨማሪ ግልጽ የሆነ ፖሊሲ ተነድፎ ወደ ትግበራ አለመገባቱ እንደሌሎች ሀገራት ዘርፉ ለምቶ ወደ ሣይንሳዊ ምርምር እንዳይሻገር እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ በጉባዔው ተወስቷል፡፡

ጉባኤው በሀገራችን ባህላዊ መድሃኒት እና ባህላዊ ህክምና ያለበትን ደረጃ፣ ከባህላዊ መድሃኒቶች እና ባህላዊ ህክምናዎች ጋር በተያያዘ የህግ ማዕቀፍ፣ የባህላዊ መድሃኒቶች ጥበቃ፣ ልማት፣ አጠቃቀምና ምዝገባ እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ በዩኒቨርሲቲውና ከተለያዩ ተቋማት በመጡ ተመራማሪዎችና መምህራን በቀረቡ ከ10 በላይ ጥናቶች ላይ መክሮ የወደፊት አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ለሚሠሩ ተግባራት እንዲረዳ ግብረ ኃይል ይቋቋማል፡፡

በጉባዔው ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከልዩ ልዩ የፌዴራልና የክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በባህል መድሃኒት ጥናት፣ ጥበቃና ማበልፀግ ዙሪያ የመጀመሪያው ዙር ጉባዔ በ2007 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት መከናወኑ ይታወሳል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት