አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የውጤታማ ትግበራ አሠራር ሥርዓት እንገነባለን!›› በሚል መሪ ቃል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚተገበረውን ግምገማዊ ሥልጠና መስከረም 08/2010 ዓ.ም ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ሥልጠናው በ3 ዙሮች ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከመስከረም 08-12፣ ነባር ተማሪዎች ከመስከረም 25-27 እና አዲስ ገቢ ተማሪዎች ከጥቅምት 2-4/2010 ዓ.ም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የመልካም አስተዳደር፣ የውጤታማነትና የህዝብ አገልጋይነት ዋና የትኩረት ነጥቦችን መነሻ በማድረግ የ2010 ትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሥልጠናው በሀገር ዓቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ ገልፀዋል፡፡

በ2009 የትምህርት ዘመን አጋማሽ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተካሄዱ የጥልቅ ግምገማ መድረኮች የተነሱ ሀሣቦችን፣ የ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እንዲሁም የመምህራንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚና እና ጥያቄ መነሻ በማድረግ የግምገማዊ ሥልጠናው ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ማስፈፀሚያ ዕቅዱ ያሳያል፡፡

በሥልጠናው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የቀረበው ‹‹መምህርነት፡ ቅድመ ሁኔታ የማይገድበው ባለአደራነት›› ሰነድ መምህራን ብቁ ዜጋን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የወላጅነትና የባለአደራነት ሚናቸውንና ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው መሆኑን ያትታል፡፡ የሀገር ልማትን ለማሳካት የትምህርትና ሥልጠና ጥራትና አግባብነትን ውጤታማ በማድረግ ሂደት የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም መምህራን  ሙያቸውን በመውደድና በማክበር እንዲሁም ሌሎችም እንዲያከብሩ በተግባር አርአያ ሆኖ በመገኘት፣ ራሳቸውንና ተማሪዎችን በማብቃት እና ጊዜያቸውንና አእምሮአቸውን ከሚሻሙ ተጨማሪ ድርጊቶች በመገደብ የትምህርት ጥራትን የማጐልበት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

‹‹የውጤታማ ትግበራ ስኬት አሠራር ሥርዓት በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን፡ ምን፣ ለምንና እንዴት››፣ ‹‹የሥነ ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ስኬቶች፣ ክፍተቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች››፣ ‹‹በጥልቅ ተሃድሶዎቻችን የተለዩ ችግሮች፣ የተቀየረው ሁኔታና ቀሪ ሥራዎች››፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2010 ዕቅድ›› እንዲሁም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች እና ሠላማዊ የትግል ስልት በትምህርት ተቋማት›› በቀጣይ የሥልጠና ቀናት የሚዳሰሱ ሰነዶች ይሆናሉ፡፡

ስልጠናውን 1966 የአስተዳደር ሠራተኞችና 1036 መምህራን በድምሩ 3002 መምህራንና ሠራተኞች በ4 የኃይል መድረኮችና በ11 የቡድን ውይይት አዳራሾች እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡