የIUC ፕሮጀክት ፅ/ቤት በጨንቻና አካባቢው የእንሰት ድህረ ምርት አሰባሰብና ጥራትን በማስመልከት ሐምሌ 15/2009 ዓ/ም በዶርዜ ሆሎኦ የእንሰት ምርምር ማዕከልና የእንሰት ፓርክ የአንድ ቀን የመስክ ጉብኝት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው እንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የIUC ፕሮጀክት ማናጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለፁት የጉብኝቱ ዓላማ በእንሰት ድህረ አሰባሰብና ጥራት እንዲሁም የጫሞ ሐይቅን ለመታደግ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በመገምገም በቀጣዩ ሊተገበሩ የሚገቡ ተግባራት ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንሰት ፕሮጀክት የእንሰት ድህረ ምርት አሰባሰብ ተመራማሪ አቶ አዲሱ ፈቃዱ የምርምር ውጤቶቹን መሠረት በማድረግ እንደገለጹት ምንም እንኳን የእንሰት ምርት ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ጥቅም የላቀ ቢሆንም ምርምሮችን ካለማድረግና ዘመናዊነትን ካለመከተል የተነሳ እንሰት መፋቅ የማህበረሰቡን ጊዜና ጉልበት ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን አንድ እንሰት ተፍቆ ለምግብነት እስከሚውል ድረስ 2 ወር ያህል መፍጀቱ፣ እንሰቱ ከተፋቀ ጀምሮ በእንሰቱ ጥራት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተሃዋሲያን መብዛታቸው እንዲሁም ሥራው የእህቶቻችንና የእናቶቻችንን ጊዜና ጉልበት መጠየቁ ለጥናቱ መነሻ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የአካባቢው ማኅበረሰብ ህይወት መሠረት የሆነውን የእንሰት ምርት አሰባሰብና ጥራት ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ከወላይታ፣ ዳውሮና ሲዳማ ዞኖች እንዲሁም ከቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲ ባላ ድርሻ አካላት የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመቅሰም እንሰት ተፍቆ ለምግብነት እስከሚደርስ ድረስ የሚወስደውን የ2 ወር ጊዜ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ተጠቅሞ ወደ 10 ቀናት በመቀነስ የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ጉልበትና የእንሰቱን ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ የምርምር ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በዞኑ ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በእንሰት የተሸፈነ መሆኑን ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ገለፃ ያደረጉት የእንሰት አጠውላጊ በሽታዎች ተመራማሪ አቶ ሳቡራ ሻራ እንሰት የሚቆረጥባቸው ስለታማ መሣሪያዎች ንፅህናቸው የተጠበቁ አለመሆን፣ ምርጥ የእንሰት ችግኞችን አለመጠቀም እና አላስፈላጊ አረሞችን በወቅቱ አለማስወገድ የእንሰት አጠውላጊ በሽታዎች እንዲስፋፉ ምክንያቶች ከሆኑት ጥቂቶቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የእንሰት ቅጠሎች መጠውለግ፣ ቢጫ መግል መሣይ በእንሰቱ አካባቢ መታየትና መሰል ምልክቶች እንሰቱ በአጠውላጊ በሽታዎች መጠቃቱን ማሳያ ሲሆኑ ምርጥ የእንሰት ችግኞችን በመትከል፣ እንሰትን ለመቁረጥ የምንጠቀማቸውን ስለታማ መሣሪያዎች ንፅህና በመጠበቅ፣ የእንሰት ችግኞቹ የሚተከሉበትን አፈር አመቺነት በመምረጥ እና አጠውላጊ በሽታዎች በእንሰቱ ላይ መታየት ሲጀምሩ ለግብርና ባለሙያዎች በማሳየት የእንሰቱ ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

የምርምሮቹ ውጤታማነት ከታየ በኋላ ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ በጉብኝቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና የዩኒቨርሲቲውና የቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በአካባቢው የተሠሩ ባህላዊ የሸክላ የቆጮ ማስቀመጫዎች፣ ከወላይታ ለተሞክሮ የመጣ የቆጮ መጭመቂያ መሣሪያ እና ከቤልጂዬም የመጡ ዘመናዊ የፕላስቲክና የብረት የቆጮ ማስቀመጫዎች ተጎብኝተዋል፡፡